የሩሲያ ነዳጅ ማዕቀብ ቢጣልበትም በከፍተኛ መጠን እየተሸጠ መሆኑ ግርምትን ፈጥራል
በሚያዝያ ወር ላይ ከምንግዜውም ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ መሸጧ ተገልጿል
በአውሮፓ ማዕቀብ የተጣለባት ሩሲያ ነዳጇን ወዴት እየሸጠችው ነው?
የሩሲያ ነዳጅ ማዕቀብ ቢጣልበትም በከፍተኛ መጠን እየተሸጠ መሆኑ ግርምትን ፈጥራል።
ሩሲያ ለጥቂት ቀናት የሚቆይ ልዩ ዘመቻ በሚል ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ ነበር በአውሮፓ ጦርነት የተጀመረው።
ይህ ጦርነት አሁን ላይ 16ኛ ወሩ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅዝቃዜ ምክንያት ቀዝቀዝ ብሎ የነበረው ጦርነት አሁን ተፋፍሞ ቀጥሏል።
ሩሲያ ጦርነቱን እንድታቆም እና ወታደሮቿን ከዩክሬን እንድታስወጣ በሚል በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት አስተባባሪነት ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥሎባታል።
የሩሲያ ዋነኛ ገቢ የሆነው ነዳጅ ሽያጭ አንዱ ሲሆን ከዋጋ ተመን መጣል ጨምሮ ለዓለም ገበያ እንዳይቀርብ ማዕቀብ ተጥሎበታል።
ይሁንና ሩሲያ ከነዳጅ የምታገኘው ገቢ እና የምትሸጠው ነዳጅ መጠኑ ጦርነት ከመጀመሩ በፊትም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ሩሲያ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከፍተኛው እለታዊ አማካኝ ምርቷ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የነበረ ሲሆን በሚያዝያ ወር ግን በቀን 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን በርሜል አምርታለች።
በማዕቀቡ ምክንያት ደግሞ 80 በመቶ የሚሆነው የነዳጅ ምርቷን ከአውሮፓ ይልቅ ወደ ሩቅ ምስራቅ ማዛወሯ ተገልጿል
ሕንድ እና ቻይና ዋነኛ የሩሲያ ነዳጅ ሸማች ሀገራት ሲሆኑ ሕንድ የሩሲያን ነዳጅ በመግባት መልሳ ለአውሮፓ ገበያ እያቀረበችው እንደሆነ ዓለም አቀፉ የነዳጅ የሀይል ኤጀንሲ በሪፖርቱ አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም የአውሮፓ ህብረት የሩሲያ ነዳጅ በሕንድ በኩል መልሶ እየቀረበለት መሆኑን ጠቅሷል።
ሕንድ በቀን ከሁለት ሚሊዮን በላይ በርሜል ነዳጅ ከሩሲያ በመግዛት ላይ ነች የተባለ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ቻይና እና ሌሎች የእስያ ሀገራት እየገዙ እንደሆነ ተገልጿል።
የሕብረቱ ውጭ ግንኙነት ኮሚሽን የሆኑት ጆሴፍ ቦሬል ሕንድ የሩሲያን ነዳጅ ልትገዛ ትችላለች ነገር ግን ገንዘቧ አውሮፓን እያወደመ እንደሆነ ልታውቅ ይገባል ሲሉ ተችተዋል።
የሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ የአውሮፓ ህብረት ፖሊሲውን ሊከልስ ይገባል እንጂ ንግድን ሊኮንን አይችልም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።