የንግድ ግንኙነቶቻችንን ወደ ብሪክስ ሃገራት እያዞርን ነው- ፑቲን
ለብሪክስ ሃገራት የሚሆን መጠባበቂያ ገንዘብን በከፍተኛ ሁኔታ ለማካበት ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛልም ብለዋል
ፑቲን የህንድ ሱፐርማርኬቶችን በሩሲያ ለመክፈት፣ የቻይና መኪኖችንም ለመሸጥ ድርድሮች በመካሄድ ላይ ናቸው ብለዋል
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድር ፑቲን ሃገራቸው የንግድ እና ሌሎች ምጠኔ ሃብታዊ ግንኙነቶቿን ወደ ብሪክስ ሃገራት እያዞረች መሆኑን ተናገሩ፡፡
ብሪክስ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ከዓመታት በፊት የመሰረቱት ጥምረት ነው፡፡ የጥምረቱ የንግድ ጉባዔ በቻይና ቤጂንግ በመካሄድም ላይ ይገኛል፡፡
በጉባዔው በቪዲዮ የተቀረጸ መልዕክትን ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ፑቲን በብሪክስ አባል ሃገራት መካከል ያለው የንግድ ግንኙነትና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልጸው ባለፉት 3 ወራት የንግድ ግንኙነቱ 38 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
የህንድ ሱፐርማርኬቶችን በሩሲያ ለመክፈት፣ የቻይና መኪኖችንም ለመሸጥ ድርድሮች በመካሄድ ላይ ናቸው ያሉት ፑቲን ወደ ህንድ እና ቻይና የሚገባው የሩሲያ ነዳጅ መጠን መጨመሩን፣ የግብርና ትብብሩ ማደጉን፣ የሃገራቸው የአይ.ሲ.ቲ ኩባንያዎች ወደ ህንድ እና በደቡብ አፍሪካ እየተስፋፉ መምጣታቸውንና የሩሲያ ሳተላይቶች 40 ሚሊዮን ለሚጠጉ ብራዚላውያን የቴሌቪዥን የስርጭት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ ባንኮች ከብሪክስ ሃገራት ጋር አስተማማኝ ዓለም አቀፍ የክፍያ መንገዶችን ለመዘርጋት በመስራት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል ፑቲን፡፡
ለቡድኑ አባል ሃገራት የሚሆን መጠባበቂያ ገንዘብን በከፍተኛ ሁኔታ ለማካበት ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡
እናም በእርግጥ የንግድ ፍሰታችን እና የውጭ ንግድ ግንኙነታችን በቀዳሚነት ወደ ብሪክስ ከዚያም አስተማማኝ ወደምንላቸው ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን በፍጥነት እየዞረ ነው ሲሉም ነው ፑቲን የተናገሩት፡፡
ፑቲን ከሰሞኑ በሞስኮው በተካሄደ የምጣኔ ሃብት ፎረም ምዕራባውያን ምንም እንኳን ዘርፈ ብዙ ማዕቀቦችን በሩሲያ ላይ ቢያዥጎደጉዱም ባሰቡት ልክ ሊያሽመደምዷት እንዳልቻሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡