የብሪክስ አባል ሀገራት የአለምን 30 በመቶ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ ናቸው
ታይላንድ የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ አቀረበች።
በተወሰኑ ኃያለን ሀገራት የሚዘወር እና የአለም ስርአትን ፍትሀዊነት ለማስጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ትብበሮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተመሰረተው ብሪክስ አዳዲስ የአባልነት ጥያቄዎች እየቀረቡለት ነው፡፡
በ2024 መጀመርያ ላይ ኢትዮጵያ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ሳኡዲ አረብያ ፣ አርጄንቲና ፣ግብጽ እና ኢራንን በአባልነት ከተቀበለ በኋላ ከ40 በላይ ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል፡፡
ባህሬን፣ ቤላሩስ፣ ኩባ፣ ፓኪስታን፣ ሴኔጋል እና ቬንዚዌላ ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አዲስ አባል ለመሆን በይፋ ጥያቄ ያቀረበችው ታይላንድ 495.4 ቢሊየን አመታዊ ጥቅል ሀገራዊ እድገት እንዳላት ይነገራል፡፡
በ1990 ከሀገሪቱ 58 በመቶ ህዝብ በድህነት ውስጥ የነበረ ሲሆን በ2020 ይህን ወደ ቁጥር ወደ 6.98 ዝቅ ማድረግ ችላለች፡፡
የታላንድ ምክር ቤት ያጸደቀው ለብሪክስ አባል የመሆን ጥያቄን የያዘው ደብዳቤ ባንኮክ በመልቲፖላር አለም እንደምታምን፣ በአንድ ወገን የሚዘወር የአለም ስርአትን እንደምትቃዎም ይገልጻል፡፡
ከ2011 ጀምሮ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ከፍ ያለ ኢኮኖሚን የምታንቀሳቀሰው የደቡብ ምስራቅ እስያዋ ሀገር የስብስቡ አባል ሀገር ብትሆን የቡድኑን አቅም ለማጠናከር ልታግዝ እንደምትችልም ገልጻለች፡፡
በፈረንጆቹ 2009 የተመሰረተው ብሪክስ የብራዚል ፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ስብስብ የያዘ ነበር።
አዳዲስ የተቀላቀሉትን አባል ሀገራትን ጨምሮ ብሪክስ በአሁኑ ወቅት የአለምን 30 በመቶ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅስ ሲሆን ለአለም አመታዊ ጥቅል እድገት 36 በመቶ ድርሻ አለው፡፡
በተጨማሪም የአለም 45 በመቶ ህዝብ ወይም 3.5 ቢልየን ህዝብ እንዲሁም የአለም 40 በመቶ የነዳጅ ዘይት ምርት በአባል ሀገራቱ ውስጥ ይገኛል፡፡
ወደ አንድ ወገን ያደላውን የምዕራባዊያን አካሄድ ፍትሀዊነት አስጠብቃለሁ የሚለው ብሪክስ የራሱ የሆነ የመገበያያ ገንዘብ ለማስተዋወቅም አቅዷል፡፡