ብሪክስ ባሳለፍነው ነሀሴ ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገራትን በአባልነት መቀበሉ ይታወሳል
ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ ብሪክስን በይፋ ተቀላቅላለች፡፡
የዓለም የምጣኔ-ሀብት ታዳጊ ሀገራት የሆኑት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ 15ተኛውን የመሪዎች ጉባኤ ባሳለፍነው ነሀሴ 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ አካሂደው ነበር።
በዚህ ጉባኤ ላይ ጥምረቱን ለመቀላቀል ካቀረቡ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ አርጀንቲና፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ሳውዲ አረቢያ እና ኢራን ተቀባይነት ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡
ብሪክስ ስድስቱን ሀገራት በአባልነት የተቀበለው ከዛሬ የፈረንጆቹ ጥር 2024 ጀምሮ እንደሚሆን በወቅቱ አሳውቆም ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ በይፋ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ለብዝሃ ወገን ግንኙነት መርሆዎች መከበር በመታገል የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ ለሰላምና ብልጽግና በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም "ነው ያስታወቀው።
እንደ ኢትዮጵያ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበው እና ተቀባይነት አግኝታ የነበረችው ደቡብ አሜሪካዊቷ አርጀንቲና ስትሆን አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጃቬር ሚሌይ ሀገራቸው ብሪክስን እንደማትቀላቀል ይፋ አድርገዋል፡፡
ባሳለፍነው ሕዳር በተካሄደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ፕሬዝዳንት ሚሌይ አርጀንቲና አዲስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደምትከተል እና ሀገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ አቋም የብሪክስ ሙሉ አባል እንድትሆን የማያደርጋት ነው ብለዋል፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራት በምዕራባውያን ኃያላን የሚመራውን ዓለም አቀፋዊ ስርዓትን ለመገዳደር እንደ አማራጭ ያዩታል።
ሀገራቱ ቡድኑ ልማት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ጥቅሞችን እንደሚከፍትም ተስፋ አላቸው።