በሀዋሳ ዩንቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ላይ አደጋ አጋጠመ
ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸዉ ይገኛል
የ2014 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መሰጠት ተጀመረ
በሀዋሳ ዩንቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ላይ አደጋ አጋጠመ።
ከ950 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚሳተፉበት የ2014 ዓ.ም ብሔራዊ ፈተና ዛሬ የተጀመረ የመጀመርያው ዙር ተፈታኞችም በዛሬው ዕለት ፈተናቸውን እንደጀመሩ ትምህርት ሚንስቴር አስታውቋል።
ይህ የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ በመሰጠት ላይ ሲሆን ዛሬ ማለዳ በሐዋሳ ዩንቨርስቲ የነበሩ ተፈታኞች አደጋ እንዳጋጠማቸው ሚንስቴሩ ገልጿል።
ትምህርት ሚንስቴር በአደጋው ዙሪያ እንዳለው በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲዉን ሁለት ካምፓሶች የሚያገናኝ ድልድይ በመፍረሱ ምክንያት ድልድዩን ሲሻገሩ በነበሩ የተወሰኑ ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
የሲዳማ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እንዳስታወቁት እስከአሁን ባለው ሂደት በጉዳቱ የአንድ ተማሪ ህይወት ሲያልፍ፣ ሁለት ከባድ ጉዳት እና ሌሎች መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸዉ ይገኛል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸዉ ይገኛልም ተብሏል፡፡
ሁኔታቸዉን ትምህርት ሚንስቴር ከዩንቨርሲቲው እና ሆስታሉ ጋር እየተከታተሉ መሆኑን የገለጸው ሚንስቴሩ ወላጆች እንዳይደናገጡ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ጉዳት የደረሰባቸዉ ተማሪዎችም በቀጣይ በሚሰጠዉ ፈተና እንደሚፈተኑ ተገልጿል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ድልድዩ የፈረሰው መሸከም ከሚችለው በላይ ተማሪ ወጥቶበት መሆኑን ገልጿል።
የሁለተኛው ዙር ማለትም የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በተመሳሳይ ፈተናቸውን በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀምሩ የትምህርት ሚንስቴር ፕሮግራም ያስረዳል።