ሁለተኛ ዙር የ2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መጠናቀቁን ት/ሚኒስቴር አስታወቀ
ፈተናው በ189 የፈተና መስጫ ጣቢያዎች ላለፉት አራት ቀናት ሲሰጥ ነበር
ትምህርት ሚኒስቴር 60 ሺህ ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን አስታውቋል
ሁለተኛ ዙር የ2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተጠናቀቀ።
በፀጥታ ችግር ምክንያት የ2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ላልወሰዱ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው ፈተና በሰላም መጠናቀቁን ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
ከጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በጸጥታ ችግር ምክንያት በመጀመሪያው ዙር በ2013 ዓም የ12ኛ ክፍል ፈተናን ያልወሰዱ ተማሪዎች ሲሰጥ ነበር።
ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋርና በቤንሻንጉል ክልል በ189 የፈተና መስጫ ጣቢያዎች የተሰጠው የመልቀቂያ ፈተና ካለምንም እንከን በሰላም መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ፈተናው ከተሰጠባቸው ቦታዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ቄለም እና ምዕራብ ወለጋ፣ በአማራ ክልል ደግሞ ሰሜን ወሎ፣ደቡብ ወሎ ፣ሰሜን ሸዋ፣ሰሜን ጎንደር፣ዋግ ኽምራ ዞኖች እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ እና በአፋር ክልል ሁለተኛው ዜር ፈተናው የተሰጠባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡
በሁለተኛው ዙር ፈተና በአጠቃላይ 60 ሺህ ተማሪዎች ለፈተና መቀመጣቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡