አሁን ላይ በእግሊዝ ጦር ውስጥ እያገለገሉ ያሉ ወታደሮች ፂም ማሳደግ እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል ተብሏል
እንግሊዝ ወታደሮቿ ፂም እንዲያሳድጉ የሚፈቅድ አዲስ የወታደር የፊት ገጽታ ፖሊሲ አወጣች።
አሁን ላይ በእግሊዝ ጦር ውስጥ እያገለገሉ ያሉ ወታደሮች ፂም ማሳደግ እንዲችሉ መፈቀዱን ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው በአዲሱ ፖሊሲ የፂም እና የሪዝ ፀጉር ንጹህ፣ በደንብ የተስተካከል እና ሁልጊዜ በእንክብካቤ መያዝ ይኖርበታል።
ይህ አዲስ ፖሊሲ የወጣው በጦሩ የፊት ገጽታ ላይ ለበርካታ አመታት የተደረጉ ውይይቶችን ተከትሎ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።
የጦሩ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የወታደሮች የፊት ገጽታ ምን መምሰል አለበት የሚለው የጦሩ ፖሊሲ ግምገም ከተደረገበት በኋላ ለውጥ ተደርጎበታል።
የጦሩ አመራሮች ለውጡን ከማድረጋቸው በፊት የግምገማውን ውጤት በጥልቀት አይተውታል።"ህዝባችንን አዳምጠን ተግባራዊ መልስ ሰጥተናል" ብሏል ቃል አቀባዩ።
ጦሩ እንደገለጸው ምንምእንኳን ፂም እና ሪዝ ቢፈቀድም፣ ኦፊሰሮች እና ወታደሮች ሙልጭ አድርገው እንዲላጩ የሚገደዱበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። የጦር መሪዎች ይህን መመሪያ ያወጡት ወደ ጦሩ አዲስ ምልምሎች እንዲገቡ ለማድረግ ነው ተብሏል።
እንደዴንማርክ፣ ጀርመን እና ቤልጄም የመሳሰሉ ሀገራት ወታደሮቻቸው ፂማቸውን እንዲያሳድጉ ይፈቅዳሉ።
በእንግሊዝም ቢሆን የሲክ፣ የእስልምና እና የራስተፈሪያን እምነት የሚከተሉ ወታደሮች ስራ እስካላደናቀፈ ድረስ እንዲያሳድጉ ቀደም ብሎ ነበር የተፈቀደላቸው።
ቢቢሲ ዘታይምስን ጠቅሶ እንደዘገበው ዋራንት ኦፊሰር ክላስ ዋን ፖውል ካርኒ ባስተላለፉት የአራት ደቂቃ የቪዲዮ መልእክት አዲሱን ፖሊሲ አስተዋውቀዋል።
ካርኒ "ይህ ውጤት ለማግኘት ንጉሱን እና ፖለቲከኞችን ጨምሮ ብዙ ባለድርሻ አካላት ማሳተፍ ስለሚገባ ከተጠበቀው በላይ ረጅም ጊዜ ወስዷል" ብለዋል።
የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስትር ባለፈው አመት ጦሩ ወታደሮች ፂም እንዳያሳድጉ መከልከሉ "የማይረባ" ነው፤ ተቋሙ ዘመናዊ መሆን አለበት የሚል ትችት አቅርበው ነበር።