የእስራኤል ሀማስ ጦርነት ሶስት ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርቶታል
ከእንቅልፉ በድንገት የነቃው የእስራኤል ወታደር ጓደኞቹን ተኩሶ መምታቱ ተገለጸ
ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ ከ83 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ጦርነት መቀስቀሱ ይታወሳል።
እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከ21 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ ከ1ሺህ 200 በላይ እስራኤላውያንም ተገድለዋል።
ወደ ጋዛ እግረኛ ወታደሮቿን ያሰማራችው እስራኤል ከሀማስ ታጣቂዎች ጋር ከባድ ውጊያ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በእርፍት ላይ የነበረ የእስራኤል ወታደርም ከእንቅልፉ ድንገት በመንቃት አብረውት እረፍት ላይ የነበሩ ወታደሮቹ ላይ መተኮሱን ጀረሰላም ፖስት ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ወታደሩ ከአስፈሪ ቅዠት በመንቃት አጋሮቹ ላይ ተኩሷል የተባለ ሲሆን እስካሁን ቁጥራቸው በይፋ ያልተገለጹ ወታደሮችን አቁስሏል፡፡
ወታደሩ ለቀናት በጋዛ ውስጥ በነበረው ከባድ ውጊያ ውስጥ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ከእንቅልፉ ድንገት በመንቃት ሊተኩስ የቻለው ከነበረበት ከባድ ጊዜ በሚገባ ባለማገገሙ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡
እስራኤል ሄዝቦላህ ጥቃቱን ካላቆመ የሊባኖስን ድንበር ጥሳ እንደምትገባ አስጠነቀቀች
ይህ ወታደር ወደ አዕምሮ ህክምና ድጋፍ ማድረጊያ ማዕከል ገብቷል የተባለ ሲሆን ምርመራ እና ህክምና ከተደረገለት በኋላ በህግ ይጠየቅ አይጠየቅ የሚባለው ይወሰናልም ተብሏል፡፡
እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም የተለያዩ ጫናዎች በመደረግ ላይ ሲሆኑ ኢራን እና የየመን አማጺዎች ደግሞ ጦርነቱ ካልቆመ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሊስፋፋ እንደሚችል በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡
የየመን አማጺያን እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት ካላቆመች በቀይ ባህር ላይ ጥቃት ማድረሱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
እንዲሁም የእስራኤል ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ የአሜሪካ መርከቦችን ማጥቃት እጀምራለሁ ሲልም አማጺያኑ አስታውቋል፡፡