በዋሸንግተን እስራኤል ኢምባሲ ፊት ለፊት ራሱን ያቃጠለው የአሜሪካ ወታደር ህይወቱ አለፈ
ወታደሩ ራሱን ያቃጠለው እስራኤል በፍልስጤም እያደረገችው ያለውን ጠጥቃት በመቃወም ነው
ወታደሩ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ምክንያት በህክምና ላይ እያለ ህይወቱ አልፏል ተብሏል
በዋሸንግተን እስራኤል ኢምባሲ ፊት ለፊት ራሱን ያቃጠለው የአሜሪካ ወታደር ህይወቱ አለፈ።
የአሜሪካ የአየር ኃይል አባሉ በትናትናው እለት በአሜሪካ በሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ ፊት ለፊት ራሱን ያቃጠለው በጋዛ እየተካሄደ ያለውን የእስራኤል ጥቃት በመቃወም ነበር፡፡
የአሜሪካ ሚስጢራዊ አገልግሎት አባላት እሳቱን ካጠፉለት በኋላ የአየር ኃይል አባሉን ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር።
አሮን ቡሽነል የተባለው የ25 ዓመቱ የአሜሪካ ወታደር በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ጉዳት ምክንያት ህይወቱ አሮይተርስ በሰበር ዜና ዘግቧል፡፡
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ግለሰቡ "በዘርማጥፋት አልተባበርም" ሲል ወታደራዊ ልብስ ለብሶ በቀጥታ በኦንላይን መልእክት አስታልፏል።
ይህን ካለ በኋላ ግለሰቡ ሰውነቱ ላይ ፈሳሽ ደፍቶ እሳት በመለኮስ "ነጻ ፍልስጤም" የሚል የለቅሶ ድምጽ አሰምቷል ብሏል ዘገባው።
ጉዳዩን የአካባቢው ፖሊስ እና ሰክሬት ሰርፊስ እየመረመሩት እንደነበር በወቅቱ ተገልጿል።
በዋሽንግተን የሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት የሚቃወሙ ሰልፎች የሚካሄዱበት ቦታ ሆኗል። እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ያለው ጦርነት በአሜሪካ እስራኤልን የሚደግፉ እና ፍልስጤምን የሚደግፉ ሰልፎች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል።
ተቃውሞዎቹ የተጀመሩት በፈረንጆቹ 2023 ጥቅምት ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ እገታ እና ግድያ ከፈጸመ በኋላ ነው።
እስራኤል በሀማስ ላይ እየወሰደችው ባለው እርምጃም እስካሁን 30 ሺህ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ባለፈው ታህሳስ ወር በአትላንታ በሚገኘው የእስራኤል ቆንስላ ፊት ለፊት አንድ ተቃዋሚ ራሷን በእሳት ማያያዟ ይታወሳል።