ግብ ጠባቂው ቡፎን ለቱርክ ጓንቶቹን በስጦታ አበረከተ
ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጁ ቡፎን ያቀረበው ጓንቶች በትዊተር እየተካሄደ በሚገኘው ጨረታ ቀርቧል
ሜሲን ጨምሮ የበርካታ ክለብ ተጫዋቾች በርዕደ መሬት አደጋው ለተጎዱ ዜጎች የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻውን ተቀላቅለዋል
ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጁ ቡፎን ከ31 ሺህ በላይ ዜጎቿን በርዕደ መሬት ለተነጠቀችው ቱርክ ጓንቶቹን በስጦታ መልክ አበርክቷል።
ቡፎን በርካታ የጎል ሙከራዎችን ያከሸፈባቸው ጓንቶቹን በጨረታ ተሽጠው በርዕደ መሬቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ለማቅረብ ይውላሉ ተብሏል።
ቱርካዊው መሪህ ደሚራል በትዊተር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው የቡፎንን ጓንቶች ጨምሮ የበርካታ ተጫዋቾች ፊርማ ያረፈባቸው መለያዎች በድረ ገጽ ለጨረታ ቀርበዋል።
በጓንቶቹ እና መለያዎቹ ጨረታ የሚገኘውን ገቢም ለቱርኩ ግብረሰናይ ድርጅት አብናፕ በማቅረብ ለተጎጂዎች እንዲደርሳቸው ይደረጋል ነው ያለው።
በአሁኑ ወቅት የሜሲ፣ ኔይማር እና ምባፔን ጨምሮ የበርካታ ተጫዋቾች መለያዎችን ለመሸጥ ጨረታው እየተካሄደ ነው።
የሮናልዶ፣ ግሪዝማን፣ ቤንዜማ እና ሌሎች ታዋቂ ተጫዋቾች መለያዎች ጨረታም ተጠናቋል።
እስካሁን በጨረታዎቹ የተገኘው ገቢ በይፋ ባይገለጽም የእግር ኳሱ መድረክ ለአንካራ አለኝታነቱን ያሳየበት እንደሆነ አናዶሉ አስነብቧል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲም የገቢ ማሰባሰብ ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሲሆን፥ በቱርክና ሶሪያ ለአስቸኳይ ድጋፍ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።
ቱርካዊው ተጫዋች መሪህ ደሚራል ከቀደሙት የክለብ አጋሮቹ እና ጓደኞቹ ጋር በመነጋገር የጀመረውን ጥረት ሌሎች ተጫዋቾችም እንደሚከተሉት ይጠበቃል።
ደሚራል ከጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጁ ቡፎን ጋር በፈረንጆቹ ከ2019 እስከ 2021 በጁቬንቱስ አብረው ተጫውተዋል።
ታዋቂው ግብ ጠባቂ ለቀድሞ የክለብ አጋሩ ጓንቶቹን በመስጠት የክፉ ጊዜ ወዳጁ መሆኑን ማሳየቱም የሚያስመሰግነው ነው ብሏል አናዶሉ በዘገባው።