ሜሲ በቱርክና ሶሪያ ርዕደ መሬት ለተጎዱ ሰዎች ልንደርስላቸው ይገባል አለ
አርጀንቲናዊው ተጫዋች በአደጋው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለይ ህጻናት ችግር ውስጥ በመውደቃቸው አፋጣኝ ትብብርን ይሻሉ ነው ያለው።
ሊዮኔል ሜሲ በቱርካዊው የክለብ አጋሩ መሪህ ደሚራል የተጀመረውን ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻም ተቀላቅሏል
በቱርክና ሶሪያ የድንበር አካባቢዎች የደረሰው ርዕደ መሬት ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን ይዟል።
በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥርም ከ33 ሺህ በላይ መድረሱ ተነግሯል።
ለአንድ ሳምንት የዘለቀው የነፍስ አድን ስራም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መታደግ የቻለ ሲሆን፥ አሁን ላይ ግን ተስፋው እየተሟጠጠ ይገኛል።
ቱርክና ሶሪያ በዚህ ፈታኝ ጊዜያቸው ሀገራት እና አለም አቀፍ ተቋማት አጋርነታቸውን እየገለጹላቸው ነው።
አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲም ለቱርክና ሶሪያ ልንደርስ ይግባል በሚል ዘመቻውን ከተቀላቀሉት ውስጥ ተመድቧል።
ሜሲ በኢንስታግራም ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ፥ “በቱርክና ሶሪያ በአሰቃቂው የርዕደ መሬት አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት እና ወላጆቻቸው ለቀናት በከባድ ሁኔታ ውስጥ ናቸው” ብሏል።
በመሆኑም ተከታዮቹ በተባበሩት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኩል ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው የጠየቀው።
ሜሲ ቱርካዊው የክለብ አጋሩ መሪህ ደሚራል የታዋቂ ተጫዋቾችን መለያዎች በመሸጥ ገቢ ለማሰባሰብ ለጀመረው ዘመቻም የፈረመበትን ማልያ በመስጠት አጋርነቱን ማሳየቱን ነው አናዶሉ ያስነበበው።
ቱርካውያን ታዋቂ የመረብ ኳስ ተጫዋቾችም የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ መክፈታቸው ተነግሯል።
ቱርክ በነፍስ አድን ስራዎች የታየው የሀገራት ትብብር በአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እና በመልሶ ግንባታ ስራዎችም እንዲታይ ጠይቃለች።
የአለም ባንክም በቅርቡ ለሀገሪቱ የአስቸኳይ ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም ስራዎች የ1 ነጥብ 78 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱ ይታወሳል።
የመንግስታቱ ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረትም ከአንካራ ጎን መቆማቸውን ለማሳየት ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
የተባባሩት አረብ ኤምሬትስ እና ህንድን ጨምሮ በርካታ ሀገራትም ምግቦች እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ወደ ቱርክና ሶሪያ መላካቸውን ቲ አር ቲ ዘግቧል።
በቱርክ ባለፈው ሳምንት በ10 ግዛቶች የደረሰው ርዕደ መሬት ከ13 ሚሊየን በላይ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አድርሷል።
ለ12 አመታት በጦርነት ውስጥ በምትገኘው ሶሪያም ከ3 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው አደጋ የበርካቶችን ህይወት ከድጡ ወደ ማጡ አስገብቶታል።