መኪናዋ ሶስት የኤሌክትሪክ ሞተር እና አንድ የነዳጅ ሞተር አላት ተብሏል
የፈረንሳዩ ቡጋቲ ኩባንያ በሰዓት 445 ኪሎ ሜትር የምትጓዝ መኪና ሰራ፡፡
ከ100 ዓመት በፊት በጣልያናዊው ኢንጅነር ኢተር ቡጋቲ የተመሰረተው ቡጋቲ የኦውቶሞቢል ኩባንያ ቅንጡ የስፖርት እና መዝናኛ መኪኖችን በመስራት ይታወቃል፡፡
ዋና መቀመጫውን በፈረንሳይ ሞልሼም ያደረገው ይህ ኩባንያ አሁን ደግሞ እጅግ ቅንጡ የሆነ አዲስ መኪና መስራቱን ይፋ አድርጓል፡፡
እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ ከሆነ አዲሱ መኪና 1 ሺህ 800 የፈረስ ጉልበት ያለው ሲሆን በሰዓትም 445 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ አዲሷ መኪና 4 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የወጣላት ሲሆን የተወሰኑ የሙከራ ስራዎች ከተደረጉ በኋላ 250 ምርቶች ለገበያ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
አዲሷ ተሽከርካሪ ሶስት የኤሌክትሪክ ሞተር እንዲሁም 1 ሺህ ፈረስ ጉልበት ያለው አንድ የነዳጅ ሞተርም እንዳላት ተገልጿል፡፡
በሚያመርታቸው መኪኖች ውበት እና ጥራት የዓለማችን ተመራጭ የሆነው ቡጋቲ ኩባንያ ከመኪኖች በተጨማሪ የአውሮፕላን ሞተሮችን፣ ባቡሮችን እና ሌሎች የመዝናኛ ምርቶችም ያመርታል፡፡
ቡጋቲ ኩባንያ አሁን ላይ 38 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ሲሆን በዓመት 320 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ እንደሚያገኝ ተገልጿል፡፡