1 ኪሎሜትር ከፍታ ያለው የጂዳው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ
በግንባታ ላይ የሚገኘው ህንጻ በዱባዩ ቡርጀ ከሊፋ ለ14 አመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን እንደሚሰብር ይጠበቃል
ከአምስት አመት በኋላ ግንባታው ዳግም የተጀመረው የጂዳ ታወር የሚጠናቀቅበት ጊዜ ግን አልታወቀም
በኤምሬትሷ ደማቅ የንግድ ከተማ ዱባይ የሚገኘው ቡርጀ ከሊፋ በሩን ለአገልግሎት ክፍት ካደረገ 14 አመታት ተቆጥረዋል።
828 ሜትር ቁመት ያለው ቡርጀ ከሊፋ የአለማችን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ክብርን ይዞ አሁንም ድረስ የዱባይ ምልክት ሆኖ ቀጥሏል።
በፈረንጆቹ ታህሳስ ወር 2004 ግንባታው ተጀምሮ በታህሳስ 2010 ተመርቆ የተከፈተው ቡርጀ ከሊፋ በበርካታ ዘርፎች ስሙን በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ማስፈር ችሏል።
ይህ የአለማችን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ አሁን ላይ የያዛቸውን ክብረወሰኖች ሊያሳጣው የሚችል ህንጻ ከወደ ጂዳ እየመጣበት ነው።
በሳኡዲ አረቢያዋ ጂዳ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የ”ጂዳ ታወር” ቁመት 1 ኪሎሜትር እንደሚደርስና 1 ነጥብ 23 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅም የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በድረገጹ አስፍሯል።
ይህ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በሰሜናዊ ጂዳ በ20 ቢሊየን ዶላር ለመገንባት የታሰበው የኢኮኖሚ ከተማ ፕሮጀክት አካል ነው ተብሏል።
በ”ጂዳ ኢኮኖሚክ ካምፓኒ” እየተገነባ ያለው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ እንደ ቡርጀ ከሊፋ ሁሉ ሆቴሎች፣ ቅንጡ አፓርትመንትና ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ቢሮዎች፣ ምግብ ቤቶችና የህክምና ተቋማት ይኖሩታል ተብሏል።
ግንባታው ከአምስት አመት በኋላ በ2023 ዳግም የተጀመረው የጂዳ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ መቼ እንደሚጠናቀቅ አልተገለጸም።
የጂዳው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በተባለው ከፍታ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በዱባዩ ቡርጀ ከሊፋ የተያዙ ሪከርዶችን መንጠቁ የማይቀር ነው።
በቡርጀ ከሊፋ የተያዙ ክብረወሰኖች በጥቂቱ፦
- የአለማችን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ - 828 ሜትር
- በርካታ ፎቆች ያሉት ህንጻ - 163 ፎቆች
- ከህንጻ ላይ በርካታ ርችቶችን በመተኮስ - በ2015 ከህንጻው አናት ሁሉም አቅጣጫ የተተኮሱ ርችቶች