የአረብ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችና መንገዶች አዲሷን መንኮራኩር ምክንያት በማድረግ በማርስ ቀለም አሸብርቀዋል
መንኮራኩሯ ወደ ማርስ ምህዋር ስትገባ በሰዓት የምትከንፍበትን ፍጥነት ከ 121ሺ ኪ.ሜ ወደ 18 ኪ.ሜ ትቀንሳለች
መንኮራኩሯ ወደ ማርስ ምህዋር የቀረበችው 7ወር ከተጓዘች በኋላ ነው
ዛሬ ማርስ ላይ ታርፋለች ተብላ ለምትጠበቀውን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንኮራኩር ደስታቸውን ለመግለጽ የአረብ ሀገራት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችና መንገዶች በሕዋ ተመራማሪዎች ቀይ ቀለም እንዳላት በሚነገርላት ማርስ ቀለም ማሸብረቃቸው ተሰምቷል፡፡
ዛሬ በማርስ ምህዋር ላይ እንደምታርፍ የምትጠበቀውና “ፕሮብ ሆፕ” የተሰኘ ሥያሜ የተሰጣት መንኮራኩሯ ለመላው አረብ ምሳሌ መሆኗን ለማመልከትና አጋርነታቸውን ለማሳየት መንገዶችና ህንጻዎች ቀይ ቀለም ባለው መብራት ደምቀው ታይተዋል፡፡
ዮርዳኖስ ታዋቂውን ጎዳናዋን ቀይ ቀለም እንዲያበራ አድርጋዋለች፡፡
የሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድም መንገዶች በማርስ ምልክት ያሸበረቁ ሲሆን ኩዌትም ተመሳሳይ ቀይ ቀለም ያለው መብራትን እያበራች መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ የጠፈር ተልዕኮ ለአረቡ ዓለም ትልቅ ስኬት እንደሆነም ሀገራቱ ገልጸዋል፡፡
መንኮራኩሯ ወደ ማርስ ምህዋር መቅረብ የቻለችው 7ወር ከተጓዘች በኋላ ሲሆን መንኮራኩሯን ለመስራት 2553 ቀናት ወይም 7 ዓመት መፍጀቱ ተገልጿል፡፡
መንኮራኩሯን ወደ ማርስ ምህዋር ስትገባ በሰዓት 121ሺ ኪሎሜትር የምትከንፍበትን ፍጥነት ፣ በራሷ የፍጥነት መቆጣጠሪያ በሰዓት ወደ 18 ኪሎሚትር እንደምትቀንስ ተገልጿል፡፡