የቻይናው ቢዋይዲ ኩባንያ “የፈጣሪ አይን” የተሰኘ ራሱን በራሱ የሚነዳ መኪና ሊሰራ ነው
ኩባንያው ለዚህ እቅዱ ዲፕሲክ ከተሰኘው ኤአይ ቴክኖሎጂ ጋር ስምምነት ፈጽሟል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/15/258-110626-whatsapp-image-2025-02-15-at-10.06.10-am_700x400.jpeg)
አዲሱ መኪና በ9 ሺህ ዩሮ ዋጋ ለገበያ ይቀርባል ተብሏል
የቻይናው ቢዋይዲ ኩባንያ ራሱን በራሱ የሚነዳ መኪና ሊሰራ ነው፡፡
ከዓለማችን ቁጥር አንድ መኪና አምራች ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ቢዋይዲ “የፈጣሪ አይን” ስያሜ የተሰጠው መኪና ሊሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው እሰረዋለሁ ያለው አዲስ መኪና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የታገዘ ሲሆን መኪናው ራሱን በራሱ ማሽከርከር የሚችል ነው ተብሏል፡፡
ከአንድ ወር በፊት ለዓለም የተዋወቀው ዲፕሲክ የተሰኘው ኤአይ ሞዴል ቢዋይዲ ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈራረማቸውም ተገልጿል፡፡
ቢዋይዲ ይህን ስምምነት ከፈጸመ በኋላ የአክስዮን ዋጋው የሁለት ዩሮ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን በዓለም ላይ ያለውን ተቀባይነትም ይጨምርለታል ተብሏል፡፡
ኩባንያው እንዳስታወቀው አዲሱን ሹፌር አልባ መኪና በ9 ሺህ 200 ዩሮ ለገበያ እንደሚያቀርበው የገለጸ ሲሆን የተሻለ ደህንነት እንደሚኖረውም አስታውቋል፡፡
የኢለን መስኩ ቴስላ ኩባንያ በአሜሪካ ገበያዎች ሹፌር አልባ መኪኖችን ሲያቀርብ የቆየ ቢሆንም ከደህንነት ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ሲነሱበት ቆይቷል፡፡
አዲሱ የቢዋይዲ ሹፌር አልባ መኪና ለደህንነት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ዩሮ ኒውስ የኩባንያውን መስራች ዋንግ ቹዋንፉን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
በድምጽ እና ሌሎች መረጃዎች እየታገዘ ራሱን በራሱ ያሽከረክራል የተባለው ይህ መኪና በዋጋም ሆነ በደህንነት የኢለን መስኩን ቴስላ ምርቶች እንዲፎካከር ተደርጎ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
ከቢዋይዲ በተጨማሪም ሌሎች የመኪና አምራች ኩባንያዎች ዲፕሲክ ኤአይ ሞዴልን ለመጠቀም ፍላጎት አሳይተዋል ተብሏል፡፡
ዲፕሲክ ኤአይ ሞዴል በአነስተኛ ወጪ ተሰርቶ ውጤታማ ሆኗል የተባለ ሲሆን በተለይም እንደ ቻትጅፒቲ እና መሰል ሞዴሎች ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተሰሩትን የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርጉ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል ተገልጿል፡፡