የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ያስደነገጠው ዲፕሲክ ማን ነው?
ከሰሞኑ መሰረቱን ቻይና ያደረገው ዲፕ ሲክ መተግበሪያ ወይም አፕ በአፕ ስቶር ላይ ይጫናል።
ይህ መተግበሪያ እንደ ጎግሉ ጀሚኒ፣ እንደ ኦፕን አይ ኩባንያው ቻትጅፒቲ እና ሌሎችም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያች ጋር ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲሰጥ ተብሎ የተዘጋጀ ነው።
የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎችን ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርገው የሰሩ ቢሆንም ይህ የቻይናው ጀማሪ ኩባንያ ግን በትንሽ ወጪ መስራቱ ተገልጻል።
ዲፕሲክ መተግበሪያ በስድስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ መሰራቱ ብቻ ሳይሆን ለተጠቃሚዎች እየሰጠ ያለው አገልግሎት ፈጣን መሆኑ በብዙዎች ተመራጭ መሆን ችሏል ተብሏል።
እንደ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ ዲፕሲክ መተግበሪያ አሁን ላይ በአፕስቶር ላይ ቁጥር አንድ ተፈላጊ ሆኗል።
ይህ መሆኑ እንደ ኦፕን አይ እና ጎግል ኩባንያዎችን ትኩረት ስቧል የተባለ ሲሆን የቴክኖሎጂ ምርቶችን እንዳትጠቀም በአሜሪካ ማዕቀብ ለተጣለባት ቻይና ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ተገልጿል።
አዲሱ መተግበሪያ አሁን ላይ ከቻትጅፒቲ እና ጀሚኒ በላይ ተፈላጊው መተግበሪያ ሆኗልም ተብሏል።
ዲፕሲክ መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች በውድ ዋጋ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ኩባንያዎች የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ሊያስገድድ እንደሚችልም ተጠቅሷል።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ የገለጸ ሲሆን ከሰሞኑ የ500 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ከኦፕን አይ ኩባንያ ጋር መፈራረሙ ይታወሳል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየዘመነ እንደሚሄድ እና በጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ በሰዎች የሚከወኑ መሰረታዊ ስራዎችን ሳይቀር ይሰራል በሚል ቴክኖሎጂ ቁጥጥር እንዲደረግበት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።