የቻይናው ቢዋይዲ ኩባንያ የዓለማችን ቁጥር አንድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሻጭ ሆነ
ኩባንያው ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከ526 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አምርቷል
የኢለን መስኩ ቴስላ ኩባንያ ለዓመታት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በመሸጥ ቀዳሚ ነበር
የቻይናው ቢዋይዲ ኩባንያ የዓለማችን ቁጥር አንድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሻጭ ሆነ፡፡
በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ ተፈላጊነታቸው እየነሰ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎም የዓለማችን አውቶሞቢል ኩባንያዎች በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ላይ ሲሆኑ የአሜሪካው እና የኢለን መስክ ንብረት የሆነው ቴስላ ኩባንያ ደግሞ ቀዳሚው ነው፡፡
ይህ ኩባንያ ከአሜሪካ በተጨማሪ በቻይና እና በሕንድ ባሉት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረቻ ስፍራዎች የዓለምን ገበያ በስፋት ተቆጣጥሮ ቆይቷል፡፡
አሁን ደግሞ የቻይናው ቢዋይዲ ኩባንያ ባለፉት ሶት ወራት ውስጥ ብቻ 526 ሺህ 409 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በዓለም ገበያ በመሸጥ ቴስላን ለመጀመሪያ ጊዜ መብለጥ ችሏል፡፡
ኩባንያው ከዚህ በተጨማሪም የሀይል ምንጫቸው ነዳጅ እና ኤሌክትሪክ የሆኑ 400 ሺህ ተሸከርካሪዎችን እንዳመረተም ተገልጿል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ የኢለን መስኩ ቴስላ ኩባንያ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ በዓለም ገበያ የሸጣቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብዛት 484 ሺህ 507 ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡
ቢዋይዲ ኩባንያ በሼንዘን ከተማ 1995 የተመሰረተ ሲሆን ከቻይና መንግስት ድጋፍ ይደረግለታል ተብሏል፡፡
የቻይና ኩባንያዎች በዋናነት የአውሮፓ እና አሜሪካ ገበያዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ የአውሮፓ ህብረት በግሞ የራሱን ኩባንያዎች ከኪሳራ ለመጠበቅ የቁጥጥር እና ድጋፍ ስልቶቹን በማጠናከር ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡