የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወለድ አልባ የሆኑና የ1 ነጥብ 1 ቢሊዬን ዶላር ዋጋ ያላቸውን አራት የብድር ስምነቶች አጸደቀ
ከሃገሪቱ የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ እና ምንም አይነት ተጓዳኝ ጫና የሌላቸው ናቸውም ነው ምክር ቤቱ ያለው
የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያላቸው ናቸው የተባለላቸው ብድሮቹ በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ እንደሆኑ ተገልጿል
ዛሬ ባካሄደው 99ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወለድ አልባ የሆኑና የ1.1 ቢሊዬን ብር ዋጋ ያላቸውን አራት የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ፡፡
የብድር ስምምነቶቹ ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተደረጉ ናቸው፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሻሻል እና ለገጠሩ ህብረተሰብ በቤተሰብ ደረጃ፣ ለማህበራዊ ተቋማት እንዲሁም ለኢንተርፕራይዞች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ የሚውል የ500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የብድር ስምምነት ነው፡፡
ሁለተኛው መሠረታዊ የአገልግሎቶች አሰጣጥን ለማሻሻልና የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማጠናከር በማሰብ የሚፈጸም የ250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የብድር ስምምነት ነው፡፡
ሶስተኛውና የ180 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላሩ የብድር ስምምነት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካኝነት የሚተገበር አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ ለማጠናከርና ለመደገፍ የሚውል ነው እንደ ምክር ቤቱ መግለጫ፡፡
አራተኛው ደግሞ የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂን በማዘመን ኢኮኖሚውን እና አጠቃላይ የመንግሥት አሰራርን ከተለመደው ባህላዊ የአሰራር ዘዴ ወደ ዲጂታል የመቀየር ስራዎችን ለማስፈጸም የሚውል የ200 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የብድር ስምምነት ነው ተብሏል፡፡
ጽህፈት ቤቱ በማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ተደግፈው ቀርበዋል ያለላቸው የብድር ስምምነቶቹ በድምሩ የ1 ቢሊየን 130 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ዋጋ አላቸው፡፡
ሁሉም ብድሮች ምንም አይነት ወለድ የማይታሰብባቸው፤ ባንኩ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብባቸው ሆነው የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱም ከሃገሪቱ የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ እና ምንም አይነት ተጓዳኝ ጫና የሌላቸው መሆኑን በማረጋገጥና በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ረቂቅ አዋጆቹ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
ምክር ቤቱ በተጨማሪነትም በአፍሪካ የመንገድ ደህንነት ቻርተር እና በተባበሩት መንግስታት የመንገድ ትራፊክ ኮንቬንሽን ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል፡፡
የስምምነቶቹ መጽደቅ ኢትዮጵያ በመንገድ ትራንስፖርት ረገድ ከጎረቤት አገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚያሳልጥ ከመሆኑም በላይ ብሄራዊ፣ አካባቢያዊና አህጉራዊ የመንገድ ደህንነት ፕሮግራሞችን በቅንጅት ለመፈጸም ያስችላል፡፡
በሀገር ደረጃ ሰፊና ሁሉን አቀፍ የሆኑ የመንገድ ደህንነት ፖሊሲዎች እንዲቀረጹ እንደሚያስችል ታምኖበት የቀረበለት ምክር ቤቱም በጥልቀት ከተወያያ በኋላ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ መወሰኑን አስታውቋል፡፡