“ሱዳን ግድቡን ለ2ኛ ጊዜ ለመሙላት ኢትዮጵያ የያዘችውን እቅድ አልተቀበለችውም”- ከፍተኛ የሱዳን ባለስልጣን
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት መርሀ-ግብር ለመከወን የሚያግዳት ምክንያት እንደሌለ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች
ሱዳን የፀጥታው ም/ቤት በግድቡ ዙርያ እንዲሰበሰብ ባለፈው ሳምንት መጠየቋ ይታወሳል
ሱዳን እየተገነባ ያለውን ግዙፉን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ለማከናወን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሀሳብ ተቃወመች።
ሮይተርስ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ያቀረበችው ሐሳብ “ተጨባጭ ያልሆነ” እና “ጊዜ ለመግዛት የቀረበ” ነው።
እንዲህ አይነቱ ሐሳብ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪዎች ጥላ ስር ሊመጣና ሁሉም ሊሳተፉበት ይገባ እንደነበርም ነው ባለስልጣኑ የገለጹት፡፡
ሱዳን ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ በጉባ ሸለቆ እየገነባችው ባለው ግድብ እና ተያያዥ ፕሮጀክቶች ጉዳይ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ም/ቤት እንዲሰበሰብ መጠይቋ ይታወሳል፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም ሳዲቅ አል-ማህዲ የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ግድቡ “በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ደህንነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ” ለመወያየት በተቻለ ፍጥነት ስብሰባ እንዲያካሂድ ጥሪ ማቅረባቸው ሮይተርስ ዘግቦ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳን ለጸጥታው ምክር ቤት ያቀረቡት ጥሪ ለአፍሪካ ህብረት ጥረት ዋጋ ያልሰጠ፣ ያላከበረና ተቀባይነት የሌለው ነው ስትል ምላሽ ሰጥታ ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪው “የተጀመረውን አፍሪካ ህብረት-መር ድርድር ወደ ጎን በመተው” የቀረበ ነው ሲል ለምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ግልፅ ደብዳቤ ጽፏል፡፡
በደብዳቤው የሀገራቱ አቋም ልክ እንደካሁን ቀደሙ ሁሉ የተቀናጀና የአፍሪካ ህብረትን ጥረት ለማጣጣል የሚደረግ ብሎም በሶስቱም ሀገራት መካከል ያለውን መተማመንን ይበልጥ የሚሸረሽር እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ያከናወነችውን የመጀመሪያውን ውሃ ሙሌት ተከትሎ በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ለማካሄድ ያቀደችውን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ሊያስቆም የሚችል ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለ ስትገልጽ ቆይታለች።
ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በዚህ ዓመት የክረምት ወራት ውስጥ ካልተከናወነ ከባድ ኪሳራን ሊያስከትልባት እንደሚችል የገለጸችው ኢትዮጵያ ድርድሩ እየተካሄደ ውሃ የመሙላት ሥራውን እንደምትቀጥል በተደጋጋሚ አሳውቃለች።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመታት በሞላው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥቅማቸውን ለማስከበር ድርድር ሲያደርጉ ቢቆዩም ሁሉን የሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ ሳይችሉ ቆይተዋል።
ሱዳንና ግብጽ ቀደም ሲል በድርድሩ ላይ ሌሎችም አካላት በአሸማጋይነት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ኢትዮጵያ የተጀመረው ሂደት በአፍሪካ ሕብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ በመግፋት ሳትቀበለው ቀርታለች።
ሱዳን የሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በተመለከተ መለሳለስ ማሳየቷና ጊዜያዊ ስምምነት እንዲደረግ ከጠየቀች በኋላ በጉዳዩ ላይ ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ጠንካራ አቋም ከያዘችው ከግብጽ በኩል አስካሁን የተሰማ ነገር የለም።
የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱን አገራት ለማሸማገል ለተራዘመ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በየትኛውም ድርድር ሁሉንም ከሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ አልቻሉም።