“ከዚህ በኋላ ትግራይ ለሚከሰት ችግር የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ አይሆንም”-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ዓለም አቀፍ ተቋማት ከዚህ በኋላ “ዕርዳታ ደረሰ አልደረሰ” በሚል መንግስትን ሊጠይቁን እንደማይገባም ተገልጿል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወታደሮችን ከመቀሌ የማስወጣቱ ሂደት ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑም ተጠቅሷል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና መከላከያ ሰራዊት በጋራ በሰጡት መግለጫ “ከዚህ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ ፤ትግራይ ክልል ለሚከሰት ችግር የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ” እንደማይሆን አስታወቁ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን ዛሬ በሰጡት መግለጫ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌ ለቆ በመውጣቱ፤ የፌዴራል መንግስት ከዚህ በኋላ በትግራይ ክልል ዙሪያ ለሚኖር ችግር ተጠያቂ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋማትም “ከዚህ በኋላ ዕርዳታ ደረሰ አልደረሰ ብለው የፌዴራ መንግስትን ሊጠይቁ” እንደማይገባ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፤ የትግራይ ክልልን በተመለከተ ሙሉ ኃላፊነቱን አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሃት እንደሚወሰድም ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት፤ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ኪሳራ እንደዳረጋት ገልጸው በልማት ሂደቱ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል፡፡
ሕወሃት የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንደጣለ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው ሱዳን፤ የኢትዮጵያን ሉኣላዊ ድንበር ጥሳ እንድትገባ አጋልጦ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ በትግራይ ክልል በተደረገ ዘመቻ፤ ከ 100 ቢሊየን ብር በላይ መውጣቱም ተገልጿል፡፡
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው እና ወታደሮችን ከመቀሌ ያስወጣው በመንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
መንግስት የተኩስ አቁም ያወጀው እና ወታደሮችን ከመቀሌ ያስወጣው፤ ሀገርን ለተጨማሪ የሀብት ብክነት ላለመዳረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ጦር በማንኛውም ጊዜ ወደ ትግራይ የመመለስ ሙሉ አቅም እንዳለውም ሚኒስትር ደኤታው አብራርተዋል፡፡
መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ባለፈው ሰኞ እለት ነበር ያስታወቀው፡፡ የመንግስትን የተናጠል ተኩስ አቁም ተመድ፣አሜሪካና የአፍሪካ ህብረት የመንግስትን ውሳኔ በአዎንታ እንደሚያዩት ገልጸዋል፡፡