ኢትዮጵያ የላፕሴት ኮሪደር ልማትን ለማፋጠን የሚረዳ ኮሚቴ ማቋቋሚያ ቢጋርን ከኬንና ደቡብ ሱዳን ጋር ፈረመች
የላፕሴት ፕሮጀክት ሦስቱ ሃገራት በፈረሙት ስምምነት ከዛሬ 10 ዓመታት በፊት መጀመሩ የሚታወስ ነው
ኮሚቴው ፕሮጀክቱን የበለጠ አጠናክሮ በመምራት ስኬታማነቱን ለማረጋገጥ ይረዳል ተብሏል
የላፕሴት (LAPSSET) ኮሪደር ልማትን ለማፋጠን የሚረዳ የሶስትዮሽ የስቲሪንግ ኮሚቴ እና የቴክካል ኮሚቴ ምስረታ ቢጋር (Terms of Reference) ተፈረመ፡፡
ቢጋሩ የተፈረመው በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ እየተከናወነ በሚገኘው የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግምገማ እና የልምድ ልውውጥ የሚኒስትሮች መድረክ ላይ ነው፡፡
በመድረኩ የሃገራቱን የትራንስፖርት ሚኒስትሮች ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የኬንያ ጠ/ሚ ራይላ ኦዲንጋ ተገኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያን፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኘው ይህ ቀጣናዊ ፕሮጀክት ሰፊ ወሳኝ እና ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ያቀፈ ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ መሳካት የምስራቅ አፍሪካን እና አካባቢውን የንግድ ትስስር በማቀላጠፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና ውህደትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር በአፍሪካ ቀጣናዊ ነጻ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር የተጀመረውን ጉዞ በእጅጉ እንደሚደግፍ ይታመናልም ነው የኢፌዲሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የሚለው፡፡
ይህ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት ሦስቱ ሃገራት በፈረሙት ስምምነት ከዛሬ 10 ዓመታት በፊት የተጀመረ ነው፡፡
ሆኖም አፈጻጸሙ ላይ መዘግየት ተስተውሏል፡፡
በዛሬው የሚኒስትሮች ውይይት እንዲመሰረት ስምምነት ላይ የተደረሰበት የስቲሪንግ ኮሚቴ የየሃገራቱን የተናጠል ጥረት አቀናጅቶ ለመምራት የሚያግዝ ነው፡፡
ስቲሪንግ ኮሚቴውን በቴክኒክ ጉዳዮች የሚደግፍ የቴክኒካል ኮሚቴ እንዲቋቋምም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ሁለቱን ኮሚቴዎች ለማቋቋም የተዘጋጀው ቢጋር በሦስቱም ሃገራት ተገምግሞ ተቀባይነት በማግኘቱ ወደ ሥራ እንዲገባ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በተደረገው መርሐ ግብር በሦስቱ ሃገራት ተወካዮች ተፈርሟል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ቢጋሩን የፈረሙት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ዳግማዊት ፕሮጀክቱን የበለጠ አጠናክሮ በመምራት ስኬታማ እንዲሆን መንግስት እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እንደሚሠሩ እና ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸው የሚቋቋመው ስቲሪንግ ኮሚቴ እና ቴክኒካል ኮሚቴ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የኬንያ ጠ/ሚ ራይላ ኦዲንጋ በበኩላቸው አጓጊ ያሉትን የላፕሴት ፕሮጄክት ለቀጣናዊ ውህደት እና የንግድ ትስስር ያለን ቁርጠኝነት መለኪያ አድርገን ልንወስደው ይገባል ብለዋል፡፡
የስምምነት ፊርማውን የተመለከተ ምስክርነታቸውን በሰጡበት የትዊተር ጽሁፋቸውም ፊርማው በደቡብ ሱዳን እና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በኩል ህንድ ውቅያኖስን ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ፤ የኬንያ ባህር ዳርቻን ከካሜሩን ባህር ዳርቻ ለማገናኘት የተያዘውን እቅድ የሚከታተል ኮሚቴ ይፋ የሆነበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡