በቡጢ ሜዳ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ያቀረበው ስፖርተኛ ምን ገጠመው?
በተፋላሚው 2 ለ 0 በተረታ ቅጽበት በ20 ሺህ ተመልካቾች ፊት ተንበርክኮ አግቢኝ በማለት መጠየቁ ወቅታዊነቱ አከራካሪ ሆኗል
ጉዳዩ የታገቢኛለሽ ጥያቄ መቅረብ ያለበት መቼ ነው? የሚልና ሌሎች ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው
ቼካዊው የማርሻል አርት ስፖርተኛ ሉካስ ቡኮቫች በቡጢ ሜዳ ለፍቅረኛው ያቀረበው የታገቢኛለሽ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም።
በተፋላሚው 2 ለ 0 በተሸነፈ ቅጽበት በ20 ሺ ተመልካቾች ፊት ነውተንበርክኮ ጥያቄውን ያቀረበው።
ሲጠብቀው በነበረው ፍልሚያ አሸንፎ ለፍቅረኛው ቀለበት ለማድረግ ያሰበው ቡኮቫች ተሸንፎም እቅዱን አልሰረዘውም።
በተሸነፈበት የቡጢ መፋለሚያ የታገቢኛለሽ ጥያቄውን አቅርቦም አሉታዊ ምላሽ አግኝቷል።
ቡኮቫች በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሲደረግበት የሚያሳየው ቪዲዮ በአጭር ጊዜ በመላው አለም ተዳርሷል።
አስተያየት ሰጪዎችም ቡኮቫች በተሸነፈበት ቅጽበት ፍቅረኛው የሰጠችው ምላሽ ይበልጥ ቅስሙን የሚሰብር ነው በሚል ሀዘኑን ተጋርተውታል።
በግጥሚያው ቢያሸንፍም የታገቢኛለሽ ጥያቄው ተቀባይነት ላያገኝ ይችል ነበር ያሉ ደግሞ ጉዳዩ ከሽንፈት ጋር የተያያዘ አይደለም በሚል ይከራከራሉ።
በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተዘዋወረ ባለው ቪዲዮ የቡኮቫች ፍቅረኛ “በመካከላችን ያ ሁሉ ነገር ከተከሰተ በኋላ ያቀረብከው ጥያቄ ተገቢ አይደለም፤ ጥያቄህን አልቀበለውም” ስትል ትደመጣለች።
የማርሻል አርት ስፖርተኛው ከዚህ ቀደም እንደወሰለተባት መናገሯንም ነው ኦዲቲ ሴንትራል ያስነበበው።
የቡጢ ፍልሚያውን ለመታደም ከገቡት ከ20 ሺህ በላይ ተመልካቾችም በሁኔታው የተደናገጡ ሲሆን፥ የቡኮቫች ደጋፊዎችም ወደ ፍቅረኛው የውሃ ኮዳዎችን ሲወረውሩ ታይተዋል።
“መልካም ሴት ብትሆን ለተሸነፈ ሰው የታገቢኛለሽ ጥያቄን ውድቅ በማድረግ ተጨማሪ ሽንፈትን አትሰጥም ነበር” ያሉ አስተያየት ሰጪዎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች አጋርነታቸውን እየገለጹለት ነው።
የፍቅረኛውን “ወስልቶብኛል” አመክንዮ የሚያነሱት ደግሞ ቡኮቫች አሸንፎም ጥያቄውን ላትቀበል እንደምትችል በመጥቀስ ትችት ከበረታባት እንስት ጎን ቆመዋል።