የአረብ መሪዎች የእስራኤል ጥቃች በአስቸኳይ እንዲቆም ሲጠይቁ ምዕራባውያን ግን ለንጹሃን የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው አንስተዋል
በግብጽ በጋዛ ጉዳይ የተደረገው 'ካይሮ ሰሚት ፎር ፒስ' ስብሰባ ያለውጤት ተጠናቋል።
በስብሰባው የተገኙት የአረብ መሪዎች እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን የአየር ድብደባ እንድታቆም ያወገዙ ሲሆን ምዕራባውያን ደግሞ ንጹሃን ከጥቃት መጠበቅ አለባቸው የሚል አቋም ማራመዳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በስብሰባው እስራኤል አልተገኘችም፣ ጥቃቱን ለማቆምም ስምምነት ላይ አልተደረሰም።
ሰብሰባውን የጠራችው ግብጽ የካይሮው ስብሰባ ተሳታፊዎች ለሰላም ጥሪ አቅርበው ያለተፈታው እና የቆየው የፍልስጤም ጥያቄ እንዲፈታ ጥረት ይጀመራል የሚል ተስፋ ነበራት።
ነገርግን መሪዎች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሳይገኙ እና የጋራ መግለጫ ሳያወጡ ስብሰባው ተቋጭቷል።
ከተቀሰቀሰ ሁለት ሳምንት የሞላው የእሰራኤል- ሀማስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ እና በከበባ ውስጥ ያሉት 2.3 ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች ለሰብአዊ ቁውስ እንዲዳረጉ አድርጓቸዋል።
እስራኤል በጥቅምት መጀመሪያ ሳምንት በጥብቅ የሚጠበቀውን ድንበሯን ጥሶ በመግባት 1400 የሚሆኑ ዜጎቿን የገደለባትን ሀማሳን በእግረኛ ወታደር ለማጥቃት እየተዘጋጀች ስለሆነ በስብሰባው የተሳተፉት ዲፕሎማቶች ውጤት ይመጣል ብለው ተስፋ አላደረጉም።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ቅዳሜ እንዳሳወቀው እስራኤል የአየር ጥቃት ከጀመረች ወዲህ 4385 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውቋል።
የአረብ መሪዎች የእሴራኤል ጥቃች በአስቸኳይ እንዲቆም ሲጠይቁ ምዕራባውያን ግን ለንጹሃን የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው አንስተዋል።
የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት ሙሀሙድ አባስ ፍልስጤማውያን አይፈናቀሉም ሲሉ ተያግረዋል።
"አንለቅም፤ አንለቅም" ሲሉ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል።
እስራኤልን የመካከለኛው ምስራቅ ዋነኛ አጋሯ አድርጋ የምታያት አሜሪካ፣ ድጋፋን ለማሳየት ሁለት ግዙፍ የጦር መርከቦችን ወደ እስራኤል ማስጠጋቷ ይታወሳል።
ሀማስ ጥቃት ከሰነዘረበት ጊዜ ጀምሮ የአጸፋ አየር ጥቃት እያካሄደችው ያለችው እስራኤል ሀማስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በማቀድ ጋዛን በእግረኛ ወታደር ለመውረር ተዘጋጅታለች።