እስራኤል በጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል በፍልስጤሙ ሃማስ ላይ የምትወስደውን እርምጃ ሀገራቸው እንደምትደግፍ ለማሳየት ቴል አቪቭ ገብተዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ዋይትሃውስ ፕሬዝዳንቱ ወደ እስራኤል ያቀኑት ጦርነቱን ለማስቆም እና የሰብአዊ ድጋፍ የሚቀርብበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው ብሏል።
የዋይትሃውስ ቃልአቀባይ ጆን ኪርቢ ባይደን ለእስራኤል መሪዎች “ከባድ ጥያቄዎችን” ያቀርባሉ ቢሉም ግልጽ እና ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ካዋቀሩት የጦር ካቢኔ ጋር ይመክራሉ ተብሏል።
ዋሽንግተን የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እንዲባባስ እንደማትፈልግ መግለጫ ብታወጣም በተግባር እየፈጸመች ያለችው ውጥረት የሚያንር እየሆነ መጥቷል።
በአውሮፕላን የጦር መሳሪያዎችን እና ከ2 ሺህ በላይ ወታደሮችን ከመላኳ ባሻገር ግዙፍ የጦር መርከቧን ወደ እስራኤል ማስጠጋቷም በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎዋን ያሳያል የሚሉ ወቀሳዎችን አስነስቶባታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በቴልአቪቭ ቆይታቸው የገቡት የድጋፍ ቃልም አሜሪካ በዚህ ጦርነት ውስጥ ሚናዋ ጎልቶ እንዲታይ ያደረገ ሆኗል፤ ጋዛ እንደ ዩክሬን ሁሉ የአሜሪካ እና የባላንጣዎቿ የእጅ አዙር ጦርነት መፋለሚያ ሜዳ እንዳትሆንም ያሰጋል።
ባይደን በዛሬው እለት በዮርዳኖስ መዲና አማን ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አባስ፣ ከግብጽ ፕሬዝዳንት እና ከዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ ሁለተኛ ጋር ለመምከር ቀጠሮ ይዘው ነበር።
ይሁን እንጂ እስራኤል በጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ጥቃት አድርሳ ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የአራትዮሽ ምክክሩ መሰረዙን ሬውተርስ ዘግቧል።
ጥቃቱን ተከትሎ በቱርክ፣ ዮርዳቦስ፣ ኢራን፣ ሊባኖስ፣ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ እና ሌሎች ሀገራት የተቃውሞ ስልፎች እየተደረጉ ነው።