የአረብ ሀገራት መሪዎች እስራኤል ጋዛ ላይ የምታደርገውን የቦምብ ጥቃት አወገዙ
በካይሮበተካሄደው የጋዛ የሰላም ጉባኤ መሪዎቹ አዲስ የሰላም ግፊት እንዲደረግ አሳስበዋል
በጉባኤው የእስራኤል የቅርብ አጋር አሜሪካ በኤምባሲ ኃላፊዋ ብቻ ተወክላለች
የአረብ መሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ ባለፉት ሁለት ሳምንት እየፈጸመች ያለውን የቦምብ ድብደባ አውግዘዋል።
መሪዎቹ የእስራኤልን ጥቃት ያወገዙት ምዕራባዊያንና ሌሎችም ሀገራት ባደረጉት የሰላም ማፈላለጊያ ጉባኤ ላይ ነው።
በስብሰባው የአረብ መሪዎች በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ግጭት ለማስቆም ጥረቶች እንዲጀመሩ ጠይቀዋል።
- ሩሲያ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ቀጠናዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቀች
- ግብጽ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ወደ ሲናይ ማፈናቀል ከእስራኤል ጋር ጦር ያማዝዘኛል አለች
የካይሮ የሰላም ጉባኤ በተሰኘው በዚህ ስብሰባ የአውሮፓ፣ የአፍሪካ እና የሌሎችም ሀገራት መሪዎች እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ተሳትፈዋል።
የእስራኤል የቅርብ አጋር እና በቀጠናው ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሁሉ ወሳኝ ተዋናይ የሆነችው አሜሪካ የካይሮ ኤምባሲ ኃላፊዋን ብቻ ልካለች።
የዮርዳኖስ ንጉስ አብዱላህ በሀማስ በሚመራው ጋዛ በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለውን እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ቤት አልባ ያደረገውን የእስራኤል ጥቃት 'ዓለም አቀፋዊ አፈና' ሲሉ አውግዘዋል።
ንጉሱ የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት በፍትዊነት እንዲፈታ አሳስበዋል።
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ፍልስጤማውያን "አይፈናቀሉም፤ መሬታቸውንም አይነጠቁም" ብለዋል።
በኢራን ይደገፋል የሚባለው የሀማስ ታጣቂ ቡድን ከሁለት ሳምነት በፊት እስራኤል ላይ ባደረሰው አስደንጋጭ ጥቃት አንድ ሽህ 400 ሰዎችን ተገድለዋል።
እስራኤል ለጥቃቱ አጻፋ ለመስጠት ሀማስን "ከምድረ-ገጽ" ለማጥፋት ቃል ገብታለች።