በሎስ አንጀለስ የተከሰተውን እሳት ለመቆጣጠር እስረኞች እንዲሰማሩ የካሊፎርኒያ ግዛት ፈቃድ ሰጥታለች
በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙት እስረኞች መጠነኛ ስልጠና ወስደው እሳቱን ለመቆጣጠር እያገዙ ነው ተብሏል
ከ135 ቢሊየን ዶላር በላይ ኪሳራ ያደረሰው የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰው አደጋ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው
በሎስ አንጀለስ የተከሰተውን እሳት ለመቆጣጠር እስረኞች እንዲሰማሩ የካሊፎርኒያ ግዛት ፈቃድ ሰጥታለች።
ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በካሊፎርኒያ ግዛት ሎስአንጀለስ የተከሰተው ሰደድ እሳት በፍጥት በመዛመት ከፍተኛ ውድመት እና ጉዳት እያስከተለ ቀጥሏል፡፡
ግዛቷ በከተማው የተከሰተውን በአይነቱ ከፍተኛ ነው የተባለውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር 4700 የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ፣ ሄሊኮፕተር እና አውሮፕላኖችን እንዲሁም ሌሎች መንገዶችን ብትጠቀምም በቂ ሆኖ አልተገኝም፡፡
ይህን ተከትሎም በተለያየ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ በጎ ፈቃደኛ እስረኞች እሳቱን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ቁጥራቸው 939 የሚጠጉት እስረኞች አደጋው ከደረሰ በኋላ በእሳት አደጋ መከላከል ላይ መጠነኛ ስልጠና በመውሰድ ከእሳት አደጋ ሰራተኞች ጋር ተቀናጅተው ሂደቱን እያገዙ ነው፡፡
እሳቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገው ጥረት አሁንም የቀጠለ ሲሆን በአካባቢው የሚገኘው መነሻውን ከውቂያኖስ ያደረገ ነው የተባለው ነፋስ እሳቱን በማባባስ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን ስራ አክብዷል፡፡
በሎስ አንጀለስ በተከሰቱ አራት ዋና ዋና ሰደድ እሳት አደጋዎች ቢያንስ 10 ሰዎች ሲሞቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
በአሜሪካ ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ ውስጥ በኃይለኛ ንፋስ እገዛ በፍጥነት እየተቀጣጠለ በሚገኝው እሳት ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከ137ሺህ በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው ተሰደዋል።
ሁለት ትላልቅ ሰደድ እሳቶች በከተማዋን ምስራቅ እና ምዕራብ አቅጣጫ አደጋን ደቅነዋል፤ ከዚህ ባለፈም እስካሁን ባለው 10ሺህ የሚጠጉ ቤቶችን እና ሕንፃዎች ወድመዋል።
ፓሊሳድስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰደድ እሳት ከ17 ሺህ 200 ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሰፊ ግዛት አውድሟል።
አደጋው የተከሰተባቸው አካባቢዎች እውቅ እና ሀብታም የሆሊውድ ተዋንያን መኖሪያ መንደሮች ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ያደረሰው ኪሳራ በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡
ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ አደጋው በህንጻዎች ፣ በመኖሪያ ቤቶች ፣ በተሸከርካሪዎች እና በሌሎችም ንብረቶች ላይ ያደረሰው ውድመት ከ135-150 ቢሊየን ዶላር ይገመታል ነው የተባለው