የኢትዮጵያ ህግ አሰሪዎች በህዝብ በዓላት ቀን ሰራተኞቻቸውን እንዳያሰሩ የሚከለክል አንቀጽ አለው?
የኢትዮጵያ አሰሪና ስራተኛ ህግ ምን ይላል?
አንዳንድ ድርጅቶች በስቅለት እና በትንሳኤ በዓላት ቀን አገልግሎት እንደሚሰጡ ማስታወቃቸው መነጋገሪያ ሆኗል
የዛሬው የስቅለት በዓል እና የመጭው እሁድ የትንሳኤ በዓል በኢትዮጵያ የቀን መቁጠሪያ መሰረት የህዝብ በዓላት ወይም ስራ ዝግ ከሚሆንባቸው እለታት መካከል ናቸው፡፡
በሁለቱ በዓላት ቀን እንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ ማስታወቃቸው በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ አንዳንዶች በህዝብ በዓል ቀን አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ለአገልግሎት ክፍት መሆን የለባቸውም ሲሉ፣ሌሎች ደግሞ ክፍት ቢሆኑም ችግር የለውም የሚሉ ሀሳቦችን እያንጸባረቁ ይገኛሉ፡፡
ለመሆኑ አሰሪ ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን በህዝብ በዓላት ቀን ማሰራት ይችላሉ?፤ ህጉስ ምን ይላል? ሲል አል ዐይን አማርኛ የሰራተኛ ጥቅም አስጠባቂ የሆነውን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽንን ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ መሰረት ስራ ዝግ በሚሆንባቸው የህዝብ በዓላት ዕለት አስገዳጅ የስራ አይነቶች ካልሆኑ በስተቀር ሰራተኞችን ስራ ማስገባት አይቻልም ብለዋል፡፡
ይሁንና ሌሎች ተቋማትም ከሰራተኞች ጋር በሚደረግ ስምምነት እና ፈቃድ መሰረት ሰራተኞችን ወደ ስራ ሊያስገቡ የሚችሉባቸው አሰራሮች አሉ የሚሉት አቶ ካሳሁን ይህ ግን ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጋር ከተስማሙ እና ተገቢውን ጥቅም የሚያገኙ እና ካለተጽዕኖ ፈቃደኛ ከሆኑ ብቻ ይሆናልም ብለዋል፡፡
ከስምምነት ውጭ ሰራተኞችን አስገድዶ ወደ ስራ ማስገባት በህግ ያስጠይቃል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሰራተኞችን አስገድደው ወደ ስራ የሚያስገቡ ተቋማት ይጠፋሉ ብለን አናምንም ሲሉም አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የ2ሺህ 201 ተቋማት ሰራተኞች መብታቸውን ለማስከበር መደራጀታቸውን የገለጹት አቶ ካሳሁን እስካሁን ከየትኛውም ተቋም ተገደው ወደ ስራ የገቡ ሰራተኞች ስለመኖራቸው ጥያቄ እንዳልቀረበላቸውም ተናግረዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ በትግበራ ላይ ያለው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የሚከበሩ የሕዝብ በዓላት ደመወዝ የሚከፈልባቸው እንደሚሆኑ ይደነግጋል፡፡
ይህ አዋጅ በወር ደመወዝ የሚከፈለው ሠራተኛ በሕዝብ በዓላት ባለመሥራቱ ምክንያት ከደመወዙ እንደማይቀነስበትም ያስገድዳል፡፡
በአሰሪ እና በሰራተኛ መካከል በሚደረግ ስምምነት መሰራት፤ አንድ ሰራተኛ ወደ ስራ የሚገባ ከሆነ በሰአት የሚያገኘው ክፍያ በሁለት ተበዝቶ በበዓሉ ቀን ለሰራበት ለእያንዳንዱ ሰአት እንደሚከፈለው አዋጁ ይገልጿል፡፡
ነገርግን አዋጁ በህዝብ በዓላት ቀን አሰሪ ድርጅቶች ለአገልግሎት ክፍት እንዳይሆኑ ወይም ስራ እንዳያሰሩ የሚከለክል አንቀጽ የለውም፡፡