ተመድ ሰራተኞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰራቸውን ሰሞኑን አስታውቋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ሰራተኞቹ ከሰሞኑ በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተመድ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎ ጥያቄ የተነሳላቸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተመድ አሊያም የሌላ ተቋም ሰራተኛ በመሆኑ የታሰረ ግለሰብ አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡
በስራው ምክንያት የታሰረ አንድም ግለሰብ እንደሌለም ቃል አቀባዩ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ የትኛውም ተቋም ሰራተኛ የሀገሪቱን ሕግ አክብሮና ጠብቆ ሊሰራ እንደሚገባ የገለጹት አምባሳደር ዲና ይህንን ካላደረገ ግን በሕግ እንደሚየቅ ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር የተመድ ወይም የአፍሪካ ሕብረት አሊያም የሌላ ተቋም ሰራተኛ ሕግ ካላከበረ እንደሚጠየቅ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕግ የጣሰ የትኛውም አካል የጎሳ፣ የጾታ እንዲሁም የሥራ ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳይገባ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል፡፡
በመሆኑም አንድ ግለሰብ የተመድ ባልደረባ በመሆኑ ወደቀኝ መነዳት ያለበትን ወደግራ ከነዳ ከተጠያቂነት አይድንም ነው ያሉት፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኛ መሆን ከሕግ በላይ እንዳልሆነም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
- የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት አሜሪካ እንደምትደግፍ ገለፀች
- የጸጥታው ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ግጭቶች ቆመው ተኩስ ለማቆም የሚያስችል ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ
የኢትዮጵያን ሕግና ስርዓት እንዲሁም በቅርቡ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማያከብሩ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡
በፌደራል መንግስት የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፤ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር የነበረውየገዥ ፓርቲ ግባሮች በመዋሃድ ብልጽግና ፓርቲን ሲመሰርቱ ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ብሎ በማፈንገጡ ነው።
ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ነው ያለውን ምርጫ ማካሄዱም የአልመግባባቱ ጡዘት ውጤት ነበር።
በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው፤ ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር፡፡
ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱ ይታወሳል። በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት ዜጎች መፈናቃላቸውንና መገደላቸውን ኢሰመኮና ሌሎች አለምአቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት በመሰንዘር፤ ሰዎች እንዲገደሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጉን መንግስት ገልጿል። አሁን ጦርነት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ህዝብ ለርሃብና ለሞት አደጋ የተዳረገ ሲሆን በ100ሺዎች የሚቆጠር ሰውም ጦርነቱን በመሸሽ እየተፈናቀሉ መሆናቸውን መንግስት እየገለጸ ይገኛሉ፡፡
መንግስት በኢትዮጵያ በሽብር የተፈረጀው ህወሓት ደቅኖታል ያለውን ሉአላዊነትን ችግር ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ለመቀልበስ ባለፈው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
በአፍካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሰጉን ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ አንድ አመት ያስቆጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡