በደቡብ ክልል በተጭበረበረ መንገድ በወር 130 ሺህ ብር ደመወዝ የሚከፈለው ሰራተኛ እንደነበረ የክልሉ ፋይናስ ቢሮ አስታወቀ
በሌሉ ሰዎችና በወረዳ አመራሮች ቤተሰብ ስም የባንክ አካውንት ተከፍቶ ደመወዝ ሲገባ እንደነበረም ተገልጿል
የራሱን ቤተሰብ በማህበር በማደራጀት ከ5 ሚሊየን ብር ያላነሰ ኃብት የመዘበረ ኃላፊም በቁጥጥር ስር ውሏል
በደቡብ ክልል በአንድ ወረዳ ጽህፈት ቤት አለአግባብ በወር 130 ሺህ ብር ደመወዝ ይከፈለው የነበረው ሰራተኛ መቀጣቱን የክልሉ የፋይናነስ ቢሮ አስታወቀ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናነስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሀዋሳ ባደረገው የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት በክልሉ በተሰሩ የኦዲት ግኝቶች ላይ ማብራሪያ እንደተሰጠው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የደቡብ ክልል የፋይናን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ አባተ፤ በክልሉ በተሰሩ የኦዲት ስራዎች እነ የተገኙ ግኝቶች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ፤ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች የተለያዩ የኦዲት ግኝቶች በምርመራ መገኘታቸውን አስታውቀዋል።
ለአብነትም በጎፋ ዞን ወይዳ ወረዳ በየጊዜው የበጀት ጉድለት እንደሚከሰት እና ከመንግስት የሚላከው እንዲሁም ከውስጥ በሚሰበሰበውም ሀብት በአግባቡ ለሰራተኞች ደመወዝ እንደማይከፈል እና የልማት ስራዎች እንደማይሰሩ በነበሩ ቅሬታዎች ላይ ምርመራ መደረጉን አስታውቀዋል።
በተደረገው ምርመራም ለረጅም ዓመታት በኃላፊነት ላይ የነበሩ፣ ከኃላፊነታቸው ሲነሱም አመጽ በማስነሳት ወደ ፋይናነስ ቢሮ ሲመለሱ የነበሩ እና የተለያዩ ሀሰተኛ ፔሮሎችን በማዘጋጀት በተለያዩ ሰዎች ስም ገንዘብ እያወጡ ሲጠቀሙ እንደበረ ተደርሶበታል።
ግለሰቦች በከተማ እና በገጠር የተለያ ቤቶችን የሰሩ እና ለየት ያለ ኑሮ ሲኖሩ እንደነበረም ኃለፊው አስታውቀዋል።
በሳውላ ከተማም ለውሃ ተቋም ግንብታ እንዲደረግ ከክልሉ የተላከውን ሀብት የፕሮጀክቱ ኃላፊ ባለቤቱን ጨምሮ የራሱን ቤተሰብ በማህበር እንዲደራጁ በማድረግ ከ5 ሚሊየን ብር ያላነሰ ኃብት በመበዝበር ወደ አዲስ አበባ መግባቱንም ኃለፊው አስታውቀዋል።
ግለሰቡ የግል ድርጅት ለማቋቋም እተንቀሳቀሰ እያለ በቁጥጥር ስር ውሎ በ9 ዓመት እስራት እና 50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት፤ ባለቤቱ 8 ዓመት እና የ50 ሺህ ብር ቅጣት፤ በወንጀሉ ተሳታፊ የነበሩ ሌሎች የማኔጀመንት አባላት እያንዳንዳቸው በ5 ዓመት እስራት መቀጣታቸውን ጠቅሰዋል።
በሀዲያ ዞን በአንዳንድ ወረዳዎች ላይ ከባንክ ጋር በመመሳጠር የ6 ሺህ 500 በር ደሞዝተኛ የሆነን ግለሰብ ላይ አንድ ዜሮ በመጨመር በየወሩ 65 ሺህ በር ደመወዝ በየወሩ ሲተላለፍለት እንደነበረ አስታውቀዋል።
እንዲሁም በአንድ ወረዳ ጽህፈት ቤት አለአግባብ በወር 130 ሺህ ብር ሲከፈለው የነበረ ግለሰብ መገኘቱን ኃላፊው አስታውቀዋል።
በዚህ ወንጀል ውስጥ ተፋታፊ የነበሩ የቢሮ ሰራተኞች እና የባንክ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገንዘቡም ለመንግስት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።
በከንባታ ዞንም በወረዳዎች ውስጥ በሌሉ ሰዎች ስም እና በወረዳ አመራሮች ቤተሰብ ስም የባንክ አካውንት ተከፍቶ ደመወዝ በየወሩ የማስገባት ስራ ሲሰራ እንደነበረ እና ይህም በጥቆማ ተደርሶበት ሰዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል።
በተመሳሳይ በሃላባ ዞንም የአንድ ጽሀፈት ቤት ኃላፊ፤ ከኃለፊነት እንደተነሳች ሲነገራት ወዲያውኑ ወደ ባንክ በመሄድ 700 ሺህ ብር ወደ ግል የባንክ አካውንቷ በማስተላለፍ ገንዘቡን ለማውጣት ስትሞክር በቁጥጥር ስር መዋሏንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ የማይገባ ስልጣን በመያዝ ሊጭበረበር የነበረ ወደ 26 ሚሊየን ብር ማዳን መቻሉን ኃላፊው አስታውቀዋል።
በወንጀል ተግባሩ የተሳተፉ በአጠቃላይ ከ3 ዓመት እስከ 14 ዓመት እስራት እንዲሁም ከ5 ሺህ እስከ 40 ሺህ የገንዘብ ቅጣት መቀጣታቸውንም አቶ ተፈራ ገልጸዋል።