
ካናዳ 51ኛው የአሜሪካ ግዛት እንድትሆን ሀሳብ ያቀረቡት ትራምፕ የቅርብ ሰው የሆነው ቢሊየነሩ በካናዳ ዙሪያ በሚሰነዝረው ሀሳብ ነው ዜግነቱ እንዲቀማ የተጠየቀው
የአለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብት ኢለን መስክ የካናዳ ዜግነት እንዲነጠቅ የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ሰፊ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡
በካናዳ የምክር ቤት አባል ካዋሊያ ሬድ እና በሌሎች ዜጎች የተጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ ሂደት ከ200 ሺህ በላይ ካናዳውያን ፊርማ እንዳረፈበት ታውቋል፡፡
የፊርማ ማሰባሰብ ሂደቱ የተጀመረው መስክ ካናዳን 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት አደርጋታለሁ ከሚሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ባለው ቅርበት እና በሀገሪቱ ፖለቲካ ዙሪያ በሚሰነዝረው ሀሳብ ነው ተብሏል፡፡
ከአምስት ቀናት በፊት በበይነ መረብ ብቅ ያለው የፊርማ ማሰባሰቢያ መስክ የካናዳን ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረር ሁኔታን ደግፎ ቆማል በሚል ከሷል፡፡
ከዚህ ባለፈም መስክ ከትራምፕ ጋር ያለው ወዳጅነት የሀገሪቱን ሉዐላዊነት ለመገርሰስ ከሚሰራ የውጭ መንግስት ጋር በግልጽ እየተባባረ መሆኑን የሚያመላክት ስለመሆኑ አብራርቷል፡፡
እነዚህ ጉዳዮች የፈጠሩት የካናዳውን ቁጣ የባለሀብቱ ዜግነት እንዲነጠቅ ለመጠየቅ አደባባይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡
ትውልደ ደቡብ አፍሪካዊው ኢለን መስክ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹን ቴስላ፣ የጠፈር ኩባንያውን ስፔስ ኤክስ እና የማህበራዊ ትስስር ገጹን ኤክስ (ትዊተርን) ጨምሮ የተለያዩ የአሜሪካ ኩባንያዎችን የሚመራ ሲሆን በእናቱ በኩል የካናዳ ዜግነት እንዳለው የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ካናዳን ወደ አሜሪካ ለማጠቃለል ያቀረቡት ሀሳብ 40 ሚሊየን ካናዳውያንን አስቆጥቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንቱ ከሀገሪቱ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ ማድረጋቸው በጎረቤታሞቹ መካከል ውጥረትን አስከትሏል፡፡
መሰል የፊርማ ማሰባሰብ ጥያቄዎች በፓርላማው ቀርበው ይፋዊ ምላሽ ወይም ውሳኔ ያገኙ ዘንድ 500 እና ከዛ በላይ ፈራሚዎችን ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ነገር ግን በ5 ቀናት ውስጥ በ100 ሺዎች ፊርማዎችን ያገኘው እና እስከ ሰኔ 20 ድረስ ይቆያል የተባለው የኢለን መስክ ዜግነት እንዲነጠቅ የሚጠይቀው ፊርማ ከሚያስፈልገው በላይ በርካታ ፈራሚዎችን ማግኘት ችሏል፡፡