ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከጣሊያን ጠ/ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጋር ተወያዩ
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በጣሊያን ይፈዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው

የዩኤኢ ፕሬዝዳትና የጣሊያን ጠ/ሚኒስትር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተወያይተዋል
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጋር ተወያዩ።
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ትናንት ምሽት ሮም የገቡ ሲሆን፤ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን በዛሬው እለት ጀምረዋል።
በዛሬው እለትም ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማዕቀፍ ውስጥ በአረብ ኤሚሬትስ እና በጣሊያን መካከል በተለያዩ የትብብር አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተዋል።
በተለይም በአረብ ኤምሬትስ እና በጣሊያን መካከል በኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ሃይል፣ የላቀ ቴክኖሎጂ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መስኮች በተሰሩ ስራዎች ላይ መክረዋል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በውይይቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የተጀመረው አረብ ኢሚሬትስ ከተመሠረተችበት የመጀመሪያ ዓመት ጀምሮ እንደሆነ እና ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የዳበረ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ላይ መድረሱን አውስተዋል።
አረብ ኢሚሬትስ የሁለቱን ሀገራት የትብብር አላማው ለማሳካት እና የሁለቱን ሀገራት እና ህዝቦች ተጠቃሚነት ወደ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ለማሳደግ ያለውን ፍላጎት እንዳላትም አንጽኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ አንፃር በ2024 የሁለቱ ሀገራት የነዳጅ ነክ ንግድ መጠን 14.1 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን፣ ከ2023 ጋር ሲነፃፀር በ21.2 በመቶ ብልጫ እንዳለው ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የጋራ ስራን በማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ መጨመር እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በምክክሩ ወቅት አረብ ኢምሬትስ በጣሊያን የ40 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ፈሰስ እንደምታደርግ ያስታወቁት ፕሬዝዳት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ፤ “ኢንቨስትመንቱ ለሁለቱ ሀገራት እና ለህዝቦቻቸው እድገት እና ብልጽግና የበኩሉን ሚና እንደሚኖረው እንጠባበቃለን” ብለዋል።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በበኩላቸው፤ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ጥቅም ለማሳካት ሀገራው ከአረብ ኤምሬትስ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በጣሊያን ይፋ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ምሽት ሮም የገቡ ሲሆን፤ ቀደም ብሎ በጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ የአረብ ኤሚሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንን በጣሊያን ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ሮም በመግታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እና ትብብር ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በበኩላው ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል እና መልካም ንግግራቸው አመስግነው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በእራት ግብዣው ላይ የአረብ ኤሚሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና የጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ አንዳቸው ለአንዳቸው ሜዳሊያ ሸልመዋል።
በዚህም ወቅት ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ለጣሊያኑ ፕሬዝዳት ሰርጂዮ ማታሬላ የተባሩት አረብ ኤምሬትስ ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ የሆነውን “የዛይድ ሜዳሊያ” አበርክተዋል።
ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላም ለፕሬዝዳት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ጣሊያን ለመሪዎች፣ ለንጉሶች እና ፕሬዝዳንቶች የምትሰጠውን ከፍተኛው ሜዳሊያ አብርክተዋል።
የሁለቱን ሀገራት ታሪክ እና ቅርስ የሚያሳዩ በርካታ ስጦታዎችንም ተለዋውጠዋል።