
ለብሔራዊ ባንኩ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በመጨመሩ የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ማደጉን ባንኩ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በነገው ዕለት በሚያቀርበው የ60 ሚሊየን ዶላር ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሁሉም ባንኮች እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ፡፡
ሐምሌ 2016 የተጀመረውን አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ረፎርም ፕሮግራም ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን የወጪ ንግድ፣ ሐዋላና የካፒታል ፍስት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ማሳየታቸውን ባንኩ አስታውቋል፡፡
ከቅርብ ወራት ወዲህ ለባንኩ የሚቀርበው የወርቅ መጠን መጨመር የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት አበራታች ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡
ከባንኩ የወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማለዘብና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ ወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሁኔታን በቅርበት በመከታተል እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ሽያጮችን የሚያካሄድ ሲሆን፤ ይህም የባንኩን የዋጋና የውጭ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስፈን ያስቀመጠው ስትራቴጂእዊ ግብ አካል ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም በነገው ዕለት የሚቀርበው የ60 ሚሊየን ዶላር ጨረታ ሰነድ ከጠዋቱ 4 እስከ 6 ሰዓት የሚቀርብ ሲሆን የጨረታው ውጤት ከቀኑ 9 ሰዓት እንሚገለጽ ነው የተነገረው፡፡