በዮርዳኖስ የመኪና ታርጋ በ1.2 ሚሊየን ዶላር ተሸጠ
"44 - 1" የሰሌዳ ቁጥር በጨረታ የተሸጠ ሲሆን፥ የሀገሪቱ ባለስልጣናት የገዥውን ማንነት ይፋ አላደረጉም
በዱባይ "ፒ 7" የሚለው ታርጋ ባለፈው አመት በ15 ሚሊየን ዶላር መሸጡ ይታወሳል
በዮርዳኖስ አንድ ቁጥር ብቻ ያለው የመኪና የሰሌዳ ቁጥር በ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ተሽጧል።
የሀገሪቱ የአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ፈቃድ ሰጪ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው ጨረታ ነው ታርጋው በውድ ዋጋ የተሸጠው።
ታክስን ጨምሮ 852 የዮርዳኖስ ዲናር (1.2 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር) ያወጣው ታርጋ ቁጥር "44 - 1" ነው።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ታርጋውን የገዛው ሰው ማንነት ይፋ አለመደረጉን ዘግበዋል።
ጥንታዊቷ ሀገር ልዩና አጭር ቁጥር ያላቸውን ታርጋዎች በቀጣይም ጨረታ እንደምትሸጥ አስታውቃለች።
አጭር ቁጥር ያላቸው ታርጋ ቁጥሮችን በመግዛት መጠቀም የባለጠጎች የሀብት ማሳያ ከሆነ ሰነባብቷል።
በዱባይ ባለፈው አመት "ፒ 7" የሰሌዳ ቁጥር በ15 ሚሊዮን ዶላር ተሽጦ የሀገሪቱን ክብረወሰን መስበሩ ይታወሳል።
በፈረንጆቹ 2008 በአቡ ዳቢ "1" የሚል የሰሌዳ ቁጥር በ52.2 ሚሊዮን ድርሃም (9.5 ሚሊየን ዶላር) ተሽጦ ክብረ-ወሰን ይዞ ቆይቷል።
ባለፈው አመት ከተሸጠው "ፒ 7" ታርጋ የተገኘው 15 ሚሊየን ዶላር ለበጎ አድራጎት እንደሚውል ተገልጾ መገለጹ አይዘነጋም።
ከዱባይ እና አቡዳቢ ባሻገር ካሊፎርኒያ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ኒውዮርክ እና ሌሎች የአለማችን ዋና ዋና ከተማዎች ልዩ የሰሌዳ ቁጥሮችን በውድ ዋጋ ሸጠዋል።
በካሊፎርኒያ ከሶስት አመት በፊት በ23.4 ሚሊየን ዶላር የተሸጠው "ኤምኤም" የአለማችን ውዱ የሰሌዳ ቁጥር ሆኗል።