በእስያ ልዩ የሰሌዳ ቁጥሮች በከፍተኛ ዋጋ እየተቸበቸቡ ነው
በዱባይ አንድ ከበርቴ ተጫራች በ15 ሚሊዮን ዶላር ልዩ የመኪና ሰሌዳ በመግዛት ከአስር ዓመት በፊት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የተያዘው ክብረ-ወሰን ሰብሯል።
ኤምሬትስ ጨረታ የተባለ ድርጅት የሰሌዳ ቁጥር "ፒ 7" ለበጎ አድራጎት አጫርቶ መሸጡን አሳውቋል።
ገቢው ለዱባይ ገዥ ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ ለዓለም አቀፍ የምግብ እርዳታ ተነሳሽነት እንደሚውል ተነግሯል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ለበጎ አድራጎት ድርጅት የሰሌላ ቁጥሮችን በጨረታ የመሸጥ ልምድ አካብታለች።
በቅርብ ጊዜው ጨረታ እ.አ.አ በ2008 በአቡ ዳቢ "1" የሚል የሰሌዳ ቁጥር በ52.2 ሚሊዮን ድርሃም በመሸጥ ክብረ-ወሰን ይዞ ቆይቷል።
የሰሞኑን የሰሌዳ ቁጥር በ15 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ ያሸነፈው ሰው ማንነት እስካሁን አልተገለጸም ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል
ከመካከለኛው ምስራቅ ባሻገርም ልዩ የሰሌዳ ቁጥሮች በከፍተኛ ዋጋ እየተቸበቸቡ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት "አር" የሚል ሰሌዳ ቁጥር በሆንግ ኮንግ 3.2 ሚሊዮን ዶላር መሸጡ ተነግሯል
ልዩ የሰልዳ ቁጥር ባለቤት መሆን እንደ ሀብት መገለጫ እየታየ መሆኑም ተነግሯል።