እስራኤል በሀይል በተቆጣጠረችው የጎላን ኮረብታ የሰፈራ ፕሮግራሟን በእጥፍ ልትጨምር ነው
ቴል አቪቭ በሶሪያ ስልጣን የጨበጡት ሃይሎች እስካሁን ለዘብተኛ ንግግር ቢያደርጉም የደህንነት ስጋቴ አልተቀረፈም ብላለች
እስራኤል በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት ነው የሶሪያን ጎላን ኮረብታዎች በሀይል የያዘችው
እስራኤል በሀይል በተቆጣጠረችው የጎላን ኮረብታ የሰፈራ ፕሮግራሟን በእጥፍ ልትጨምር ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ "ጎላንን ማጠናከር እስራኤልን ማጠናከር ነው፤ በተለይ በዚህ ወቅት በጣም አስፈላጊ ነው፤ አጥብቀን እንቀጥልበትና እናሰፍርበታለን" ብሏል።
እስራኤል ከአንድ ሳምንት በፊት በሽር አላሳድን አስወግዶ ስልጣን የተቆጣጠረው ሃይል እስካሁን ለዘብተኛ አቋሙን ቢገልጽም ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንዳለባት ስትገልጽ ቆይታለች።
የሶሪያ ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያዎች "በአክራሪዎች እጅ እንዳይገባ" በሚልም ከ350 በላይ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች።
ጦሯን ከጦርነት ነጻ ወደሆነው (በፈር ዞን) አስገብታም የአምስት የሶሪያ መንደር ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማስጠንቀቋን ሬውተርስ አስታውሷል።
በ1967ቱ የእስራኤልና አረቦች ጦርነት (የስድስት ቀናት ጦርነት) አብዛኛውን የጎላን ኮረብታ ክፍል የተቆጣጠረችው እስራኤል በ1981 የግዛቷ አካል አድርጋ ሰፈራ ጀምራለች።
በ2019 የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በጎላን ላላት ሉአላዊ መብት እውቅና ቢቸሩም አብዛኛው የአለማቀፉ ማህበረሰብ ግን ድጋፍ አልሰጣትም።
ኔታንያሁ በሶሪያ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ከተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ መምከራቸውን ተናግረዋል።
በውይይታቸውም ከሶሪያ ጋር ግጭት ውስጥ መግባት አንፈልግም ያሉት ኔታንያሁ፥ በድንበራችን ላይ የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አንፈቅድም ማለታቸውም ተዘግቧል።
የእስራኤል መንግስት በትናንትናው እለት በጎላን የሰፈራ ፕሮግራሙን በእጥፍ ለማሳደግ የ40 ሚሊየን ሸክል (11 ሚሊየን ዶላር) በጀት ማጽደቁም ቴል አቪቭ በጎላን ይዞታዋን ለማስፋት ማቀዷን አመላክቷል።
ሳኡዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ዮርዳኖስ የእስራኤልን ውሳኔ "ወረራን ለማስፋፋት ያለመ" ነው በሚል አውግዘውታል።
እስራኤል በተቆጣጠረችው የጎላን ኮረብታ 31 ሺህ የሚጠጉ እስራኤላውያን ሰፍረዋል፤ አዲሱ እቅድም አሃዙን ወደ 60 ሺህ ያሳድጋል ተብሏል።
በሶሪያ የአሳድ አገዛዝን ለመጣል የተካሄደውን ፈጣን ዘመቻ የመራው የሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድን መሪው አህመድ አል ሻራ (አቡ ሞሀመድ አል ጎላኒ)፥ እስራኤል በሶሪያ ጥቃት ለመፈጸም ሀሰተኛ ሰበብ መደርደሯን ቀጥላለች ሲል ወቅሷል።
ሶሪያን ዳግም መገንባት ላይ ትኩረት ስለምናደርግም ከእስራኤል ጋር አዲስ ግጭት ውስጥ መግባት አንፈልግም ማለቱንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የእስራኤል የጎላን አካባቢ እንቅስቃሴ ግን ሀገራቱን ጦር ሊያማዝዝ እንደሚችል ከወዲሁ ስጋት ፈጥሯል።