ያደጉት ሀገራት የሚገዙት የካርበን ክሬዲት ምንድን ነው? አፈጻጸሙስ?
በቅርቡ ይፋ የተደረገ ጥናት የካርበን ክሬዲት ገዥዎች የደን መጨፍጨፍን መቀነስ አልቻሉም ብሏል
በደን ጭፍጨፋ ምክንያት በየአመቱ 40 ቢሊየን ቶን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ይለቀቃል
የካርበን ክሬዲት ወይም የካርበን ልቀት ድርሻ ሽያጭ ሀገራትና ኩባንያዎች በካይ ጋዝን መቀነስ ካልቻሉ በሚል የቀረበ አማራጭ ነው።
በዋናነት የበለጸጉትና በካይ የሆኑት ሀገራት ካርበን ክሬዲት በመግዛት ካርበን ዳይ ኦክሳይድ እና ሌሎች በካይ ጋዞችን እንዲለቁ የሚፈቅደው አማራጭ በብክለት ለሚጎዱ ሀገራት ሊደረግ የሚገባን ድጋፍም ያስቀምጣል።
የካርበን ክሬዲት ግዙፍ ኩባንያዎች እስከ 1 ቶን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ እንዲለቁ ይፈቅዳል፤ ቀስ በቀስ ልቀታቸውን እንዲቀንሱና የሚለቁትን ካርበን ከከባቢ አየር ላይ እንዲያስወግዱም ያሳስባል።
የካርበን ክሬዲት ተጠቃሚዎች በታዳጊ ሀገራት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለማገዝ የሚውል መዋዕለ ንዋይ ያፈሱ ዘንድም ይጠየቃሉ።
የደን መጨፍጨፍን የሚያስቀሩ፣ ስነምህዳር እንዲያገግም የሚያደርጉ እንዲሁም ብዝሃህይወትን የሚመልሱ ስራዎችን እንዲያከናውኑም አለማቀፍ ስምምነት ተደርሷል።
የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋቾች ግን የካርበን ልቀት ድርሻ ሽያጭ ወይም ካርበን ክሬዲት በካይ ጋዞችን በብዛት የሚለቁ ሀገራትና ኩባንያዎች ብክለታቸውን እንዲገፉበት እንደመፍቀድ ይቆጥሩታል።
በአንጻሩ እንደ ሬድ ፕላስ ባሉ ፕሮግራሞች የሚደገፉ የአየር ንብረት ጥበቃ ስራዎች እንዲጠናከሩ የካርበን ገበያው መጠነኛም ቢሆን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው በሚል የሚከራከሩ አሉ።
በቅርቡ በሳይንስ ጆርናል ላይ የወጣ ጥናት ግን የካርበን ክሬዲት የገዙ ኩባንያዎች የደን ጭፍጨፋን መቀነስ እንዳልቻሉ አመላክቷል።
ጥናቱ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ታንዛኒያ፣ ኮሎምቢያ፣ ካምቦዲያ እና ፔሩ በመንግስታቱ ድርጅት የሬድ ፕላስ ፕሮግራም የሚደገፉ 18 የካርበን ክሬዲት ፕሮጀክቶችን ዳሷል።
በጥናቱ የተካተቱትና የከባቢ አየር ብክለትን ይቀንሳሉ የተባሉት ፕሮጀክቶች የደን መጨፍጨፍን በመቀነስ ረገድ ያከናወኑት ስራ ከሚጠበቅባቸው ከ6 በመቶ አይበልጥም ተብሏል።
በደን ጭፍጨፋ ምክንያት በየአመቱ 40 ቢሊየን ቶን ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃል።
ይህም ምድራችን እያሞቃት ነው የሚለው ጥናቱ ካርበን እንዲለቁ የተፈቀደላቸው ኩባንያዎች በታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረትን ለመጠበቅ መከወን ያለባቸውን ስራ በሚገባ እያከናወኑ አይደለም ብሏል።
ከፍተና የካርበን ክሬዲት ለማግኘትም የተጋነነ የደን ልማት እና ተያያዥ ስራዎችን ሪፖርት እንደሚያደርጉ ነው የጠቆመው።
የጥናቱ ዋና ጸሃፊ አንድሬስ ኮንቶሊዮን የካርበን ገበያው የሚመራበት መንገድ ግልጽነት የጎደለውና ለቁጥጥርም አመቺ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።
አለም በአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዋ እየጠነከረ ሲሄድ የካርበን ክሬዲት ገበያውም ተጧጦፎ መቀጠሉ ብክለቱን ይበልጥ እንዳያንረው ስጋታቸውንም ያክላሉ።