አለም እውን በ2050 ከካርበን ልቀት ነጻ ትሆናለች?
እቅዱ ፖለቲካዊ ግነት ይታይበታል የሚሉ ተንታኞች፥ በየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታ እንዲቃኝ አሳስበዋል
በነዳጅ ኩባንያዎች ላይ ያለው የአመለካከት ክፍተትም አሁንም ለእቅዱ ስኬታማነት ፈተና ይሆናል ተብሏል
በአለማቀፍ ደረጃ በ2050 የበካይ ጋዝ ልቀትን ዜሮ ለማድረስ የተያዘው ግብ ተፈጻሚነት እንደየሀገራት እና ኩባንያዎች ነባራዊ ሁኔታ ዳግም ሊጤን እንደሚገባው ተገለጸ።
ኦይል ፕራይስ የተሰኘው ድረገጽ እንዳስነበበው በርካታ የነዳጅ ኩባንያዎች እቅዱ የመሳካቱ ነገር ላይ ጥርጣሬ አላቸው።
ሼል እና ኤግዞሞቢል ስጋታቸውን ካነሱ የነዳጅ ኩባንያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የነዳጅ ኩባንያዎቹ የ2050ው ግብ እንዳይሳካ እንቅፋት ይሆናል ያሉት የማህበረሰቡ ወጪያቸው ከፍ ለሚሉ ከብክለት የጸዱ የሃይል ምንጮች ያለው ዝግጁነት አነስተኛ መሆንን ነው።
ምድርን በ2050 ከበካይ ጋዝ ልቀት ነጻ የማድረጉ እቅድ እያንዳንዱን አባዋራ እና አማዋራ ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳርግ ሪፖርቱ ያነሳል።
እቅዱን ለማሳካት እያንዳንዱ ሰው በየቤቱ ጣሪያ ላይ ከጽሃይ ሃይል የሚያመነጩ ፓኔሎችን እንዲሰቅል ይጠበቃል።
ይህም እንደ መዳብ ያሉ ማዕድናት በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውሉና ሰዎችን ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉ እንደማይቀር ይታመናል።
ይሁን እንጂ ወጪው የታዳሽ ሃይል ሽግግሩና የበካይ ጋዝ ልቀትን ዜሮ የማድረስ እንቅስቃሴው ከሚያስገኘው ዘርፈብዙ ጥቅም አንጻር እጅግ ያነሳና የማይነጻጸር መሆኑን “ማቴሪያል ወርልድ” የተሰኘውን መጽሃፍ ለንባብ ያበቁት ኢዲ ኮንወይ ተናግረዋል።
ኦይል ፕራይስ በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ የማድረስ ግቡ በአብዛኛው ፖለቲካዊ ግነት የተጫነው መሆኑን ያነሳል፤ በየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታ ካልተቃኘም የመሳካቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ይላል።
በተለይ የነዳጅ አምራች ኩባንያዎች እና ሀገራትየገቡትን ቃል በሚገባ መፈጸም አለመቻላቸውንም በማብራራት።
የሀገራትን አራምባ እና ቆቦ የሆነ እሳቤም ብሪታንያን እና ኖርዌይን አብነት አድርጎ ያነሳል።
ብሪታንያ የአውሮፓ የአረንጓዴ ፋይናንስ ማዕከል ለመሆን ስትቃረብ፤ ኖርዌይ ግን 17 ቢሊየን ዩሮ ለሚያወጡ 19 የነዳጅ ፍለጋ ፕሮጀክቶች ፈቃድ ሰጥታለች።
ኦስሎ በአውሮፓ አስተማማኝ የነዳጅ ክምችት ያላት ሀገር ለመሆን ስትጥር በ2050 ከካርበን ልቀት ነጻ አለምን የመፍጠር ግብ እንዳትዘነጋው ያሳስባ ይላል የኦይል ፕራይስ ድረገጽ ዘገባ።