ተቃዋሚዎች የመሃማት ኢድሪስ ዴቢ ስልጣን መቆናጠጥ “መፈንቅለ መንግስት”ነው ብለውታል
አዲሱ የቻድ የሽግግር መንግስት የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢን በመግደል ከተከሰሱት አማፅያን ጋር አልደራደርም አለ ፡፡
የወታደር ቤቱ ቃል አቀባይ ጄኔራል አዜም በርማንዶአ አጎማ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ አመጺያኑ “በሊቢያ ውስጥ ቅጥረኛ ሆነው ካገለገሉ በርካታ ጂሃዲስቶች እና አዘዋዋሪዎች” ጋር ለመተባበር ይፈልጉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
“በዚህ የቻድን እና መላው አከባቢን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ገጥሞ ባለበት ወቅት፤ ከህግ አውጭዎች ጋር ለሽምግልና ወይም ለድርድር የሚሆን ጊዜ አሁን አይደለም”ም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡
በፈረንሳይኛ ቅፅል ስሙ“ፋክት” በመባል የሚታወቀው አማጺ ቡድን ፤የዴቢ ልጅ መሃማት ኢድሪስ ዴቢ የሚቃወሙ ሌሎች የታጠቁ ቡድኖችን እንደሚቀላቀል በትላንትናው ዕለት አስታውቋል ፡፡
ከአመጺ ኃይሎች ጋር የመደራደር ፍላጎት እንደሌለው የገለፀው የሽግግር መንግስት፤ አሁን በመከላከያ እና በፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት ከቻድ ዋና ከተማ በጣም ርቀው “በኒጀር ክልል ተሰባስበው በሚገኙ ትናንሽ የጠላት ቡድኖች”ላይ በአየር ኃይል የታገዘ ወታደራዊ ጥቃት ማካሄድ እንደጀመረም ነው የአሶሽትድ ፕሬስ ዘገባ የሚያመላክተው፡፡
ይሁን እንጂ የአማጺ ቡድኑ ቃል አቀባይ ጥቃት ቢሰነዘርብንም “ተስፋ አልቆረጠም”ብለዋል ፡፡
የቻድ አማጺያን መሰረታቸውን በደቡብ ሊቢያ ያደረጉ ሲሆን በምርጫ ቀን ወደ ቻድ ተመልሰው እንደገቡ ይታመናል ፡፡
ለ30 ዓመታት ያክል ስለጣን ላይ የቆዩት ዴቢ ለተጨማሪ የስልጣን ዘመናት በትረ ስልጣን ጨብጠው እንዲቆዩ የሚያስችላቸው ከፍተኛ ድምፅ ማግኘታቸው ተከትሎ ፤በማግስቱ ግንባርን በሚጎበኝበት ጊዜ መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም ታድያ የፕሬዝዳንት ዴቢን ህልፈት ተከትሎ የልጃቸውን የስልጣን መቆናጠት “መፈንቅለ መንግስት” ነው በሚል በተቃዋሚዎች ዘንዳ ከፍትኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ድርጊቱን የሚቃወም ሰልፍ እንዲወጣ ጥሪ በማቅረብም ጭምር ፡፡
የቀድሞው የቅኝ ገዢ ኃይል ‘ፈረንሳይ’ የወታደሮችን ድርጊት ከመተቸት የተቆጠበች ይመስላል፡፡የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ሳምንት በዴቢ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል ፡፡
ፈረንሳይ የጸረ-ሽብር ተግባራት ለማከናወን ቻድ ውስጥ እንደ ዋና መስርያ ቤት የምትጠቀምበት ወታደራዊ ካምፕ መኖሩ እንዲሁም ቻድ በሰሜናዊ ማሊ ላለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለተባበሩት መንግስታት ወታደሮች ማቅረቧ ለፈረንሳይ መለሳለስ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይነሳል፡፡