የቻድ ፕሬዝደንት መገደላቸውን ተከትሎ ሀገሪቱን የሚመራ የሽግግር ም/ቤት ተቋቋመ
በቻድ የተካሔደውን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለ6ኛ ጊዜ ማሸነፋቸው ይፋ በተደረገበት በዛሬው ዕለት ነው ፕሬዝደንቱ የተገደሉት
የሽግግር ም/ቤቱ በሟቹ ፕሬዝደንት ልጅ መሐመድ ኢድሪስ ዴቢ እንደሚመራ ተገልጿል
እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት ቻድን የመሩት ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ መገደላቸውን የሀገሪቱ መከላከያ ዛሬ ሚያዝያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም አስታውቋል፡፡
ከትናንት ጀምሮ በዋና ከተማዋ ኒጃሚና ላይ ጠንካራ ውጊያ እንደነበር እና ፕሬዝደንቱ ከአማጺያን ጋር በመዋጋት ላይ የነበሩ ወታደሮችን በመጎብኘት ላይ እያሉ ተመትተው ከቆሰሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ህይወታቸው ማለፉን ከሀገሪቱ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የቻድ አማጺያን በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ዋና ከተማዋ ኒጃሚና ከትናንት ጀምሮ በመቅረብ ላይ እንደነበሩ የሚገልጹ መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡
የፕሬዝደንቱን ሞት ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ የሀዘን ጊዜ ታውጇል፡፡ የሀገሪቱ ሁሉም ድንበሮች እንዲዘጉም ተወስኗል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት እና ፓርላማ እንዲበተን የወሰነው የሀገሪቱ ጦር የሽግግር ምክር ቤት አቋቁሟል፡፡ ቀጣይ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሀገሪቱ ጦር ለ18 ወራት የሚቆየውን የሽግግር ጊዜ እንዲመራም ተወስኗል፡፡ የሽግግር ምክር ቤቱን የሟቹ ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ ልጅ መሐመድ ኢድሪስ ዴቢ እንደሚመሩት ነው መከላከያው ያስታወቀው፡፡
የቻድ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ መግለጫ ሲሰጡ
ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ፣ በቻድ ምርጫ እስካሁን ከተቆጠረው 80 በመቶ ድምጽ ከ79 በመቶ የሚሆነውን በማግኘት ማሸነፋቸው በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኖ ነበር፡፡