ለ30 ዓመታት ቻድን የመሩት ፕሬዝዳንት ኢድሪስ በቀጣዩ ምርጫም ሊወዳደሩ ነው
የፕሬዘዳንቱ ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ሲጠበቁ የነበሩ ሦስት እጩዎች ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል
ፕሬዝዳንት ኢድሪስ በሳህል ቀጠና ያለውን የጽንፈኞች እንቅስቃሴ በመግታት የተሻለ ስራ እንደሰሩ ይነገርላቸዋል
ላለፉት 30 ዓመታት ቻድን በፕሬዘዳንትነት የመሩት ኢድሪስ ዴቢ ከአንድ ወር በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ አስታወቁ።
የቻድ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እ.ኤ.አ. የፊታችን ሚያዝያ 11 እንዲካሄድ የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ቀን የቆረጠ ሲሆን አገሪቱን ላለፉት 30 ዓመታት በፕሬዘዳንትነት የመሩት ፕሬዘዳንት ኢድሪስ ዴቢ ለስድስተኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል። ለቀጣዩ ምርጫም የምረጡኝ ቅስቀሳ ባለፈው ሀሙስ የተጀመረ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ እና ፓርቲያቸውም ቅስቀሳቸውን ጀምረዋል፡፡
ፕሬዘዳንቱ በአገሪቱ ዋና ከተማ ኢንጃሚና ስታዲየም ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር ህዝቡ በአንድነት እነዲቆም ጥሪ አቀርበዋል።
በዚህ ምርጫ ላይ ለፕሬዘዳንት ኢድሪስ ዋነኛ ተፎካካሪ የሚባሉ ሦስት የፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እጩዎች ደረሰብን ባሉት ተጽዕኖ ምክንያት አስቀድመው ራሳቸውን እንዳገለሉ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል። ተቀናቃኝ እጩዎቹ ፍትሓዊ እና ግልጽ የሆነ ምርጫ ይካሔዳል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ጭምር ገልጸዋል፡፡
የተቃዋሚዎቻቸው አዝማሚያ ያላማራቸው ፕሬዝዳንት ኢድሪስ በስታዲየሙ ንግግራቸው “ዲሞክራሲ ከረብሻ ጋር ተመሳሳይነት እንደሌለው ህዝቡ ማወቅ አለበት” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ አክለውም “ያንን የሚያምኑ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አለባቸው ” ነው ያሉት፡፡
ፕሬዘዳንት ኢድሪስ ዴቢ ቻድን እንደ ጎርጎሮሲያን ዘመን አቆጣጠር ከ1990 ጀምሮ በመምራት ላይ ሲሆኑ በሳህል ቀጠና ያለውን የጽንፈኞች እንቅስቃሴ በመግታት በአንጻራዊነት የተሻለ ስራ እንደሰሩ ይነገርላቸዋል።
ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ አገር ቻድ ከሊቢያ ፣ ሱዳን ፣ ናይጀሪያ ፣ ኒጀር እና ካሜሩን ጋር የምትዋሰን ሲሆን ከ120 በላይ ቋንቋዎቸን የሚናገሩ 16 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ናት።