የቀድሞው የኒጀር ሀገር ውስጥ ሚኒስትር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን አስታወቁ
ባዙም ከተሰጠው ድምጽ 55.75 በመቶ በላይ የሚሆነውን በማግኘት እንዳሸነፉ ገልጸዋል
በኒጀር ምርጫ የገዥው ፓርቲ ተወካይ የሆኑት መሐመድ ባዙም ማሸነፋቸውን አስታወቁ
የቀድሞው የኒጀር የውጭ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ ሚኒስትር መሐመድ ባዙም በሀገሪቱ የተደረገውን ምርጫ ማሸነፋቸው አስታወቁ፡፡
ገዥውን ፓርቲ ወክለው ለምርጫ ቀርበው የነበሩት ባዙም በምርጫው ከተሰጠው ድምጽ 55.75 በመቶ በላይ የሚሆነውን በማግኘት ማሸነፋቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
የገዥው ፓርቲ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት በአውሮፓውያኑ 1996 በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ተወግደው የነበሩት መሐመድ ኡሳማኔ ይፋ የተደረገው ውጤቱ ትክክል አለመሆኑንና ምርጫው መጭበርበሩን ገልጸዋል፡፡
በኡስማኔ የምርጫ ቅስቀሳ ቢሮ ውጭና በሌሎች የኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ አካባቢ ደጋፊዎቻቸው ጎማ በማቃጠል ተቃውሞ አሰምተዋል፤ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን አስቃሽ ጭስ ተጠቅሟል፡፡
ኡስማኔ ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ባቀረቡት ክስ ላይ የምርጫ ኮሚሽኑ እስካሁን ያለው ነገር የለም ተብሏል፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑ ፕሬዘዳንት ኢሳቅ ሶና ምርጫው 8 ሰዎች በሞቱበት ሁለት ጥቃት እክል ገጥሞት ነበር ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ገዥው ፓርቲ ምርጫውን ማሸነፉን ቢያውጅም ውጤቱ በሀገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት መረጋገጥ እንዳለበት ሪዩተርስ ዘግቧል፡፡ የገዥው ፓርቲ ተወካይ ሆነው የቀረቡትና ምርጫውን ማሸነፋቸውን ያወጁት መሐመድ ባዙም በኒጀር በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተመረጡ መሪ የሥልጣን ርክክብ በማድረግ የመጀመሪያ ይሆናሉ ተብሏል፡፡