ሆኖም የሃገሪቱ ዋና አማጺ ቡድን ስምምነቱን አልተቀበለውም ተብሏል
በኢድሪስ ዴቢ ማሃማት የሚመራው የቻድ ወታደራዊ የሽግግር መንግስት ከተቃዋሚዎቹ ጋር ንግግር ሊያደርግ ነው።
ወታደራዊ መንግስቱ እና ተቃዋሚዎቹ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ተፈራርመዋል።
የሽግግር መንግስቱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ማሃማት በዚህ ወር መጨረሻ ለሚጀመረው ብሔራዊ ምክክር ከ40 ከሚልቁ ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር ዛሬ ሰኞ በኳታር ዶሃ ተፈራርመዋል።
ምክክሩ ከ15 ቀናት በኋላ ይጀመራል። ይህን ተከትሎም የስምምነቱ አካል የሆኑ ወገኖች ከዚያ ቀድመው ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል።
ሆኖም 'FACT' በሚል ምህጻረ ቃል የሚጠራው ቀዳሚ የሃገሪቱ አማጺ ቡድን ስምምነቱን አልተቀበለም። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን ቡድኑ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አልገለጸም።
'FACT ቻድን ከ1990ዎቹ ጀምሮ ከመሩት ከፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ግድያ ጀርባ እጁ እንዳለበት ይነገራል።
ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ከዓመት በፊት በሃገሪቱ ተቀስቅሶ በነበረ አመጽ መገደላቸው ይታወሳል።
በአባቱ እግር ተተክቶም ነው የ38 ዓመቱ ልጃቸው ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ማሃማት በወታደራዊ የሽግግር ፕሬዝዳንትነት ቻድን እየመራ ያለው።
ሆኖም ተቃዋሚዎቹ ማሃማት ለማድረግ በታሰበው ምርጫ እንደማይሳተፍ ማረጋገጫ እንፈልጋለን ሲሉ ከአሁን ቀደም ጠይቀዋል።
ይህን ተከትሎም የሽግግር መንግስቱ በ18 ወራት ውስጥ የሲቪል መንግስትን ለማቋቋም የያዘው ውጥን ይሳካ ይሆን የሚል ጥያቄን አስነስቷል።