ለሶስት አመት በወታደራዊ አገዛዝ የቆየችው ቻድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እያካሄደች ነው
የሽግግር ፕሬዝዳንቱ ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ በምርጫው የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል
ነዳጅ ሻጯ ሀገር በ1960 ከፈረንሳይ ነጻነቷን ካወጀች ወዲህ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አልቻለችም
ቻድ ለሶስት አመት ከቆየችበት ወታደራዊ አገዛዝ ለመውጣት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እያካሄደች ነው።
የመካከለኛው አፍሪካዋን ሀገር ለ30 አመት የመሩት ኢድሪስ ዴቢ በ2021 በአውደ ውጊያ ላይ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ልጃቸው ጀነራል ማህማት ኢድሪስ ዴቢ የሽግግር ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆኖ በማገልገል ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ጀነራል ማህማት በዛሬው እለት እየተካሄደ በሚገኘው ምርጫ እየተፎካከሩ ሲሆን፥ የማሸነፍም ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
8 ነጥብ 5 ሚሊየን መራጮች ድምጽ ለመስጠት በተመዘገቡበት ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱኬስ ማስራ የዴቢ ዋነኛ ተቀናቃኝ እንደሚሆኑም ነው ፍራንስ 24 ያስነበበው።
10 የሀገሪቱ ፖለቲከኞች በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ላይ እንዳይሳተፉ የሀገሪቱ የህገመንግስት ጉዳዮች ምክርቤት መወሰኑ የሚታወስ ነው።
ያያ ዲሎ የተባሉት የዴቢ ተፎካካሪ በየካቲት ወር 2024 በኢንጃሚና መገደላቸውም በምርጫው ነጻና ፍትሃዊነት ላይ ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል።
አሜሪካ ጦሯን ከቻድ በጊዜያዊነት በምታስወጣበት ወቅት የሚካሄደው ምርጫ የዴቢን ስረወመንግስት የሚያስቀጥል እንጂ ለውጥ ለሚፈልጉ ቻዳውያን ለውጥ ይዞ አይመጣም የሚሉ ተቺዎችም አሉ።
እንደሌሎቹ በወታደራዊ ጁንታ የሚተዳደሩ የአፍሪካ ሀገራት ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ጋር ግንኙነቷን ያላቋረጠችው ኢንጃሚና የፓሪስ ጦር የሚገኝባት ብቸኛዋ የሳህል ቀጠና ሀገር ሆናለች።
ከሩሲያ ጋር ትብብሯን ያጠናከረችው ቻድ 18 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሲሆን፥ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀችበት 1960 ወዲህ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንዳልቻለች ይነገራል።
በቅድመ ምርጫው ከታዩ ጉዳዮች አንጻርም የዛሬው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ተብሎ እንደማይጠበቅ ተቃዋሚዎችና የሲቪል ማህበራት ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በወታደራዊ መሪዎች ከሚተዳደሩ የአፍሪካ ሀገራት ምርጫ በማካሄድ ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗ በራሱ ጥሩ ጅምር ነው ይላሉ የጀነራል ማህማት ኢድሪስ ዴቢ ደጋፊዎች።