ቻድ አራት የሱዳን ዲፕሎማቶች ከሀገሪቱ እንዲወጡ አዘዘች
ኢንጃሚና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) የጦር መሳሪያ እንዲያስገባ ፈቅዳለች በሚል ከሱዳን ጦር ወቀሳ ቀርቦባታል
ከ500 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ጦርነትን ሸሽተው በቻድ በስደት ይገኛሉ
ቻድ አራት የሱዳን ዲፕሎማቶች ሀገሬን ለቀው ይውጡ ማለቷ ካርቱምን ማስቆጣቱ ተነግሯል።
የሱዳን ጦር ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ እና የሉአላዊ ምክርቤቱ አባል ያሲር አል አታ የሰጡት አስተያየት ነው የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያሻከረው።
ያሲር አታ ኢንጃሚና ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲሸጋገር የአውሮፕላን ማረፊያዎቿን ክፍት አድርጋለች የሚል ወቀሳን አሰምተዋል።
ይህን የወታደራዊ አዛዡን አስተያየት ተከትሎም የቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የማያስፈልጉ ሰዎች” ያላቸውን አራት የሱዳን ዲፕሎማቶች በ72 ስአት ውስጥ ከኢንጃሚና እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገልጿል።
ቻድ በሀገሪቱ የሚገኙት የሱዳን አምባሳደር ለቀረበው “መሰረትአልባ ክስ” ይቅርታን እንዲጠይቁ ጠርታ ነበር።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ አል ሳዲቅ ይቅርታ አንጠይቅም፤ ለቻድም ማስረጃዎችን ማቅረብ እንችላለን” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ሚኒስትሩ የሱዳን ጦር ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥን አስተያየት መድገማቸው ኢንጃሚናን አበሳጭቶ ዲፕሎማቶቹ እንዲባረሩ አድርጓል ነው የተባለው።
የቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “መሰል አስተያየቶችን አንታገስም” ያለ ሲሆን ድንበር የሚጋሩት ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አደጋ ውስጥ መግባቱ እየተዘገበ ነው።
ካርቱምም መሰል እርምጃ እንደምትወስድ ይጠበቃል።
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ድራሽ ሃይሉ ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ 540 ሺህ ሱዳናውያን ድንበር አቋርጠው ቻድ መግባታቸው ይታወሳል።