ቻድ “በአስማተኞች” ሊፈጸም የነበረን የመንግስት ግልበጣ ማክሸፏን አስታወቀች
የሀገሪቱ የደህንነት ተቋም፥ “ኤም3ኤም” የተባለ ቡድን በአስማተኞችና ጠንቋዮች ታግዞ መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂድ ነበር ማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል
ከ80 በላይ የቡድኑ አባላትም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል
የማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ቻድ በአይነቱ ለየት ያለ የመንግስት ግልበጣ ሙከራን አክሽፌያለሁ አለች።
ኢንጃሚና ፊልም የሚመስል እና በአስማተኞች እና ጠንቋዮች የሚታገዝ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራን ነው አከሸፍኩ ያለችው።
የሀገሪቱ የወታደራዊ ደህንነት ተቋም እንዳስታወቀው “ኤም3ኤም” የተሰኘ ቡድን “የሀገሪቱን ደህንነት የሚያናጋ ድርጊት” ሲፈጽም ነበር ብሏል።
የቻድ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አብዱል ራህማን ካላም በበኩላቸው፥ “ይህ ቡድን ነፍጥ ታጥቆ ሳይሆን በአስማትና በጥንቆላ አቢዮት ለማስነሳት ሲሞክር ነበር፤ ለሶስት ጠንቋዮችም የዶሮ፣ በግና ፍየል እንዲሁም የሰው ልጅ ጭንቅላት በመስዋዕትነት አቅርቧል” ነው ያሉት።
በ”ኤም3ኤም ንቅናቄ” ቡድን መሪው ቤት በቦርሳ ውስጥ የሰው ልጅ ጭንቅላት መገኘቱንም ባወጡት መግለጫ ጠቁመዋል።
የቻድ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በአስማት መንግስት ሊገለብጥ ነበር የተባለው ቡድን መሪ ሌተናንት ኮሮምታ ሌቫና ይባላሉ።
ሌተናንት ኮሮምታ በቻድ መንግስት ስለቀረበባቸው “ጠንቋይና አስማተኞችን ቀጥረህ መንግስት ለመገልበጥ አሲረሃል” ክስ እስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም።
የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ግን የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ክሱ ድራማ ነው ብለውታል።
ከ”ኤም3ኤም” ንቅናቄ ጋር ግንኙነት ነበራቸው፤ ለጥር 13 2024 ሊካሄድ በነበረው የመንግስት ግልበጣም ለመሳተፍ መክረዋል በሚል 80 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም የቻድ ጀነራሎች አጀንዳ ለማስለወጥ የወሰዱት እርምጃ እንጂ የሚታመን አይነት አይደለም በሚል ተቃውመውታል።
ቻድን ለ30 አመታት የመሩት ኢድሪስ ዴቢ በ2021 በጦር ግንባር ላይ ከተገደሉ በኋላ ልጃቸው ጀነራል ማሃማት ኢድሪስ ዲቤ ኢንጃሚናን በመምራት ላይ ይገኛል።
ጀነራል ማሃማት ኢድሪስ ዲቤ በ18 ወራት ውስጥ ምርጫ ከተደረገ በኋላ ስልጣን እንደሚያስረክቡ ቢያሳውቁም እስካሁን በስልጣን ላይ ናቸው።
በዚህ አመት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲፎካከሩም ገዥው ፓርቲ “ፓትሪዮቲክ ሳልቬሽን ሙቭመንት” እጩ አድርጎ መርጧቸዋል።
የሰሞኑ የ”አስማተኞች” የመንግስት ግልበጣ ክስና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃም ስልጣን ለመቆናጠጥ የሚፎካከሩ ጀነራሎችን ፍጥጫ ለመሸፈን የተቀነባበረ ነጭ ውሸት ነው የሚሉ አስተያየቶች ከተቃዋሚዎች ጎራ ተደምጠዋል።