ቻን በሀገር ውስጥ ሊግ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ቅድመ ዝግጅት ሞሮኮ ካዛብላንካ ገብቷል።
በሁለት ዙር ወደ ሞሮኮ ያቀኑት ዋልያዎቹ በቆይታቸው ከሞሮኮ አቻቸው ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ያስታወቀው።
ቡድኑ የመጀመሪያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታው ታህሳስ 29 2015 እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፥ ከሁለት ቀናት በኋላ ሁለተኛው ግጥሚያ ይደረጋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሩዋንዳ አቻውን 1 ለ 0 በማሸነፍ በታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ ለቻን አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ማረጋገጡ ይታወሳል።
ዋልያዎቹ በቀጣዩ ሳምንት በአልጀሪያ በሚጀመረው 7ኛው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ከአዘጋጇ አልጀሪያ፣ ሊቢያ እና ሞዛምቢክ ጋር በምድብ 1 ተደልድለዋል።
ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን ከሞዛምቢክ ጋር ጥር 5 2015 የምታደርግ ሲሆን፥ በቀጣዩ ቀን ከአልጀሪያ ጋር የምትፋለም ይሆናል።
ወደ ሞሮኮ ያቀኑት ዋልያዎቹ በሶስተኛ የቻን ተሳትፏቸው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በሞሮኮ የስምንት ቀናት ልምምድና ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ።
አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለውድድሩ ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው እንደነበር የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ጥሪ የተደረገለት አጥቂው ጌታነህ ከበደ በተፈጠረ አለመግባባት ራሱን ከብሄራዊ ቡድኑ ማግለሉን መግለጹ አይዘነጋም።
ጌታነህ ከ2001 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ክብረወሰን ሆኖ የተመዘገበ 33 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
የ2023 የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል
ምድብ 1
አልጀሪያ
ኢትዮጵያ
ሊቢያ
ሞዛምቢክ
ምድብ 2
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
ኡጋንዳ
ኮቲዲቯር
ሴኔጋል
ምድብ 3
ሞሮኮ
ሱዳን
ማዳጋስካር
ጋና
ምድብ 4
ማሊ
አንጎላ
ሞሮታንያ
ምድብ 5
ካሜሮን
ኮንጎ ብራዛቪል
ኒጀር
የ2023 የቻን የአፍሪካ ዋንጫ በአልጀሪያ አራት ከተሞች ከጥር 5 2015 እስከ ጥር 27 2015 ይካሄዳል።
አልጀርስ፣ ኮንስታንቲን፣ ኦራን እና አባባ ውድድሩን የሚያስተናግዱ ከተሞች ናቸው።