የዓለም ዋንጫ ያዘጋጀችው ኳታር ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ
አሰልጣኙ ከኳታር ብሔራዊ ቡድን ጋር ጥሩ የሚባሉ ጊዜያት ማሳለፋቸው ገልጸዋል
የኳታር ፕሬዝዳንት ሼክ ሃማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ስፔናዊው አሰልጣኝ ላደረጉት ጥረት አመስግነዋል
የኳታር አሰልጣኝ ፊሊክስ ሳንቼዝ ከኋላፊነታቸው መልቀቀቃቸው የኳታር እግር ኳስ ማህበር አስታወቀ፡፡
ማህበሩ ሳንቼዝ ከኋላፊነታቸው የለቀቁት ውላቸውን በትናንትነው እለት ታህሳስ 32 ቀን 2022 ማለቁንና እንደገና ላለማዳስ በጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ነው ብሏል፡፡
የ47 ዓመቱ አሰልጣኝ ሳንቼዝ አዳዲስ እድሎች የማየት ፍላጎት እንዳላቸው ለመረዳት ችለናልም ነው ያለው የኳታር እግር ኳስ ማህበር፡፡
አሰልጣኙ ከኳታር ብሔራዊ ቡድን ጋር ጥሩ የሚባሉ ጊዜያት ማሳለፋቸው ገልጸዋል፡፡
"ላለፉት 5 ከ ግማሽ ዓመታት ከኳታር ብሔራዊ ቡድን ጋር የነበረኝ ቆይታ በህይወት ውስጥ አንድ ጊዜ የሚገኝ እድል ነበር" ያሉት አሰልጣኙ “ኳታር፣ ህዝቦቿ እና ኳሷ ምንጊዜም በልቤ ውስጥ ይኖራሉ። አሁን ሌሎች የቡድኑን ኋላፊነት እንዲወስዱ እና አዳዲስ እድሎችና ፈተናዎች መፈለግ ያለብኝ ጥሩ ጊዜ ነው” ሲሉም ተማግረዋል፡፡
የኳታር ፕሬዝዳንት ሼክ ሃማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ስፔናዊው አሰልጣኝ ላደረጉት ጥረት አመስግነዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኳታር እግር ኳስ ማህበር በሳንቼዝ ምትክ የብሔራዊ ቡድኑን ስራ ማን እንደሚወስድ በቅርቡ አስታውቃለሁ ብሏል፡፡
አሰልጣኙ በቅርቡ የዓለም ዋንጫን በተሳካ ሁኔታ ያዘጋጀችውን የኳታር ብሔራዊ ቡድን ይዘው ወደ ዓለም መድረክ ቢቀርቡም ውጤት ማስመዝገብ ተስኗቸው ከምድባቸው ቀድመው መሰናበታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ኳታር በዓለም ዋንጫው በኢኳዶር፣ በሴኔጋል እና በኔዘርላንድ ሽንፈትን አስተናግዳ በምድብ ሀ ግርጌ ስታጠናቅቅ አንድ ጎል ብቻ ነበር ማስቆጠር የቻለችው፡፡