ቻይና በታይዋን ጉዳይ የሚስተዋለውን ጣልቃ ገብነት ለመከላከል “ጠንካራ እርምጃ” እወስዳለሁ ስትል አስጠነቀቀች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቻይናን ውህደት ለማደናቀፍ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ በሂደት ይፈርሳል ብለዋል
ቻይና በታይዋን ጉዳይ “አሜሪካ ጣልቃ እየገባች ነው” የሚል ተደጋጋሚ ክስ ስታቀርብ ትደመጣለች
ቻይና በታይዋን ጉዳይ የሚስተዋለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል “ጠንካራ እርምጃ” እወስዳለሁ ስትል አስጠነቀቀች፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባዳረጉት ንግግር፣ ቤጂንግ ለደሴቲቱ ነጻነት ተብሎ የሚደረገውን ማንኛውንም የውጭ ድጋፍ እንከላከላለን ብለዋል፡፡
ዋንግ ዪ “የነጻነት ተገንጣይ እንቅስቃሴዎችን በቆራጥ ውሳኔ ለመዋጋትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም በጣም ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ አለብን" ሲሉ መናገራቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የቻይናን ዳግም ውህደት ለማደናቀፍ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ በሂደት መፈራረሱ አይቀርምም ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡
ቻይና በታይዋን ጉዳይ አሜሪካ ጣልቃ እየገባች ነው የሚል ተደጋጋሚ ክስ ስታቀርብ ትደመጣለች፡፡
በቅረቡ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቻይና “ጥቃት ከፈጸመች” የአሜሪካ ኃይሎች ታይዋንን ይከላከላሉ ያሉበት አጋጣሚ፤ የቤጂንግ ባለስልጣናትን ያስቆጣ አጋጠሚ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ቻይና የፕሬዝዳንት ባይደን አስተያየት ዋሽንግተን በታይዋን ላይ ያላትን “ፖሊሲ በእጅጉ የሚጥስ ነው” ነበር ያለችው፡፡
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ጀ ባይደን ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ በቅርቡ በነበራቸው የስልክ ቆይታ፣ አሜሪካ የታይዋንን የህልውና ጥያቄን የሚቀይር የተናጠል እርምጃን አጥብቃ እንደምትቃወም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ የተበሳጩት የቻይናው ፕሬዝዳንት ባይደን “የአንድ ቻይናን መርህ” እንዲያከብሩ በማሳሰብ፤ የታይዋን ጉዳይ በእሳት እንደመጫወት ነው ሲሉም ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል።
“ማንኛውም በእሳት የሚጫወት መቃጠሉ አይቀርም” ሲሉ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጆ ባይደንን የወረፉበት አጋጠሚ አይረሳም፡፡
ያም ሆኖ ዋሽንግተን እንደፈረንጆቹ በ1979 ከታይዋን ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብታቋርጥም፤በጉዳዩ ላይ ዋሽንግተን ቁርጥ ያለ አቋም ሳትይዝ ለረዥም ጊዜ በዲፕሎማሲያዊ ዥዋዥዌ መጓዟንና ታይዋንን በተለያየ መልኩ ስታግዝ በማገዝ ላይ መሆኗ ይነገራል።
በቅርቡ የአሜሪካ ምክር ቤት ያጸደቀውና ከታይዋን ጋር ከስምምነት የተደረሰበት የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ በአሜሪካ ታይዋን መካከል ያለው አጋርነት የሚያሳይ እንደሆነም በርካታ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡