ቻይና በዩክሬን ለተፈጠረው ቀውስ “ዋና ቀስቃሽ” አሜሪካ ናት አለች
በሩሲያ የቻይና አምባሳደር ዣንግ "የአሜሪካ የመጨረሻ ግብ ሩሲያን በተራዘመ ጦርነት ማዳከም ነው" ብለዋል
ቻይና እና ሩሲያ በመካከላቸው “ገደብ የለሽ አጋርነት” እንዲኖር በመስማማት በጋራ እየሰሩ ያሉ ሀገራት ናቸው
በታይዋን ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር መካረር ውስጥ የገባችው ቻይና፤ በዩክሬን ለተፈጠረው ዩክሬን ቀውስ “ዋና ቀስቃሽ” አሜሪካ ናት አለች፡፡
በሞስኮ የቻይና አምባሳደር ዣንግ ሃንሁዊ ረቡዕ ታትሞ ከወጣው የሩስያ መንግስት የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፤ ዋሽንግተን በኔቶ የመከላከያ ህብረት ተደጋጋሚ መስፋፋት በማድረግና እና ዩክሬንን ከአውሮፓ ህብረት ጋር ለማስማማት ለሚፈልጉ ሃይሎች ድጋፍ በመስጠት ሩሲያን ወደ ጥግ እየገፋቸው ነው በማለት ከሰዋል።
አምባሳደር ዣንግ "ዋሽንግተን የዩክሬን ቀውስ ዋና አነሳሽ እና ቀስቃሽ ናት፤ አሁንም በሩሲያ ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አጠቃላይ ማዕቀብ መጣልንና ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ቀጥላበታለች" ሲሉ መናገራቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
"የእነሱ (አሜሪካውያን) የመጨረሻ ግባቸው ሩሲያን በተራዘመ ጦርነት እና በማዕቀብ ማዳከም ነው"ም ብለዋል፡፡
የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በየካቲት ወር ወደ ቤጂንግ ተጉዘው ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር ባደረጉት ምክክር በሀገራቱ መካካል “ገደብ የለሽ አጋርነት” እንዲኖር መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡
የሀገራቱን ወቅታዊ ግንኙነት በተመለከተ የተጠየቁት አምባሳደር ዣንግም የሲኖ-ሩሲያ ግንኙነት "በታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ሀገራቸው የሩሲያን ሉዓላዊነት እና ደህንነትን እንደምትደግፍ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት በቅረቡ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ቤጂንግ “በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ፈቃደኛ ነች”ም ነበር ያሉት ዢ፡፡
የሩሲያ እና የቻይና ወዳጅነት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የትብብር ምሳሌ መሆኑን ፕሬዘዳንት ፑቲን ከወራት በፊት ከቻይናው አቻቻው ጋር በነበራቸው የበይነ መረብ ውይይት መናገራቸውም የሚታወስ ነው።
ሀገራቱ በወታደራዊ፣ በቴክኖሎጂ፣ በጠፈር ሳይንስ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በሌሎች ሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በጋራ እንደሚሰሩ ይታወቃል፡፡