አንቶኒ ብሊንከን ቻይና ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ትብብር ለማቋረጥ የወሰደችው እርምጃ “ኃላፊነት የጎደለው” ነው አሉ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “የቤጂንግ አጸፋዊ እርምጃ አሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚቀጣ ነው” ብለዋል
ብሊንከን፤ አሜሪካ ከቻይና ጋር ያላትን የግንኙነት ቻናል አሁንም ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተናግረዋል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ቻይና ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ትብብርና ቁልፍ የሆኑ የመገናኛ መንገዶችን ለማቋረጥ የወሰደችው እርምጃ "ኃላፊነት የጎደለው",ነው አሉ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ በአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት የተበሳጨቸው ቤጂንግ የጦር አውሮፕላኖቿንና መርከቦቿ በታይዋን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችላቸው ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማቆም አደንዛዥ እጾች፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች እና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በስምንት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የወሰደችው አጸፋዊ እርምጃ አሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚቀጣ መሆኑም ነው የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡
በፍሊፕንስ ማኒላ የሚገኙት ብሊንከን በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ "የአየር ንብረት ትብብርን ማገድ አሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለምን በተለይም በማደግ ላይ ያሉትን ሀገራት የሚቀጣ ነው።በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ልዩነት ምክንያት ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ትብብሮችን እንደ መያዣ መጠቀም የለብንም" ሲሉ መደመጣቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን መዋጋት ጉዳይ በሁለቱ ሃያላንና ትላልቅ የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀት ባላቸው ሀገራት መካከል ቁልፍ የትብብር መስክ ሆኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል ።
ቻይና በታይዋን ዙሪያ እየፈጸመች ያለውን አደገኛና በቀጠናው አለመረጋጋት ሊፈጥር የሚችል ድርጊትን በተመለከተ ዋሽንግተን ከአጋሮቿ እየሰማች ነው ያሉት ብሊንከን ፤ “ ዋሽንግተን ጉዳዩን በምታስተናግድበት መንገድ እያስተናገደች ጸንታ ትቀጥላለች” ብለዋል፡፡
ደርጊቱ ቻይና ለሰላማዊ መፍትሄ ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ ወደ ሃይል መጠቀም እንደሄደች የሚያመላክት መሆኑም ተናገርዋል፡፡
ያም ሆኖ፤ ችግሮችና ውጥረቶች በሚከሰቱበት ወቅት ንግግር የተሸለ አማራጭ በመሆኑ አሜሪካ ከቻይና ጋር ያላትን የግንኙነት ቻናል አሁንም ክፍት ሆኖ ይቆያል ሲሉም አክለዋል፡፡